አስራ ስድስተኛው የቲቢ ምርምር ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል
አመታዊ ብሔራዊ የቲቢ ምርምር ጉባኤ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መደረጉ ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ አገራች ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት እና የተለያዩ ግጭቶች ምክንያት በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመቶች እና የጤና ተቋማት መስተጓጎል፤ የህዝብ መፈናቀል፤ የድርቅ መስፋፋት እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያቶች በቲቢ በሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ላይ የተመዘገቡ ስኬቶች እንዳይቀለበሱ በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
በየአመቱ በሚካሄደው የቲቢ ምርምር ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ የምርምር ሥራዎች የቲቢ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አገራች ኢትዮጵያ የቲቢ በሽታ ስርጭት ለመግታትና ቲቢ ለማጥፋት ዘመናዊ የምርመራ መሳሪያዎችን በጤና ተቋማት በማስገባት አገልግሎቱ ተደራሽ በማድረግና በየአምስት አመቱ የሚተገበር እቅድ በማዘጋጀት እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡