የአፍሪካ ህብረት ልማት ኤጀንሲ-ኔፓድ የሚኒስትሮች መድረክ ለተዋልዶ ጤና ትኩረት በመስጠት ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማፋጠን እና የአፍሪካን ስነ-ህዝብ አቅም መጠቀም” በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የአፍሪካ ሃገራት ሚኒስትሮች ልምድ የሚለዋወጡበት እና በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን መግባባት ላይ የሚደርሱበት መድረክ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በመድረኩ የመክፈቻ ንግግራቸው ያስረዱ ሲሆን፤ ጉባኤው በዋናነት የስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረቱን ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ማፍሰሷን ያስታወሱት ዶ/ር መቅደስ፤ በዚህም የእናቶች እና ህጻናት ህልፈትን መቀነስ መቻሉን እና አጠቃላይ የጤና ስርአትንም ማሻሻል መቻሉን አብራርተዋል፡፡ የአፍሪካ ሃገራት የሃገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ አፍሪካ በጤና ዘርፍ እራሷን እንድትችል መስራት ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ያጋጠሙ የፋይናንስ ክፍተቶችን የሃገር ውስጥ ሃብትን በማሳባሰብ እና ከአጋሮች ጋር በትብብር በመስራት መቅረፍ እንደሚገባ አክለዋል፡፡