Articles

በሶማሌ ክልል በድርቅ የተጎዱ አከባቢዎች ለሚገኙ ጤና ተቋማት አገልግሎት የሚውል ሰላሳ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያዩ መድሀኒቶች፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል። 

donation

በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰሀረላ አብዱላሂ የተመራ ከጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት እና የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት የተውጣጣ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ቡድን በሶማሌ ክልል በድርቅ የተጎዱ አከባቢዎች ለሚገኙ ስድስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና ስድስት ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት የሚውል የመድሀኒት፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የህክምና ቁሳቁሶችን  አስረክቧል። 


ሰላሳ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት መድሀኒት፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የህክምና ቁሳቁሶች በሁለት ዙር በክልሉ ጤና ቢሮ በኩል ወደ ጤና ተቋማት የሚደርስ ርክክብ ተደርጓል። 


በቀጣይም በድርቅ ለተጎዱ የኦሮሚያ፣ ደቡብ ብ/ብ/ህ/ክ እና ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የምግብና መድሀኒት አቅርቦት እንደሚቀጥል ወ/ሮ ሰሀረላ ገልጸዋል።

በጤና ሚኒስቴር እና ግብርና ሚኒስቴር የሚመራ የዓለም ጤና ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅትን እንዲሁም ዩኒሴፍን ያካተተው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በዛሬው እለት በኦሮሚያ ክልል በድርቅ የተጎዳዉን የቦረና ዞንን ጎብኝቷል። 

Borena

በዱቡሉቅ ወረዳ የዱቡሉቅ ጤና ጣቢያ አጣዳፊ የምግብ እጥረት ህክምና መስጫ ማዕከልንና የመጠጥ ውሃ ጥራት ቁጥጥርን እንዲሁም በድርቁ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን ቡድኑ ተመልክቷል። 


በጉብኝቱም ቡድኑ ከዞኑ አመራሮች ጋር በወቅታዊዉ ሁኔታና የድንገተኛ ድጋፍ አሰጣጥን አስመልክቶ ውይይት ያደረገ ሲሆን በድርቁ የተጎዱ እና የጤና እና የምግብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸዉን ዜጎች ለማከም፤ ለመደገፍ የሚዉሉ ከአለም ጤና ድርጅት የተገኙ 31 ሜትሪክ ቶን የድንገተኛ ህክምና ቁሳቁስ ድጋፎችንም አበርክቷል።


በቀጣይም ክፍተት ባለባቸው ላይ የፌደራል መንግስትና አጋር አካላትና ድጋፉን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በፌደራል ጤና ሚኒስቴር እና ግብርና ሚኒስቴር የሚመራ የዓለም ጤና ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅትን ያካተተ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በድርቅ የተጎዳዉን የሱማሌ ክልል ሸበሌ ዞንን ጎብኝቷል።

Somali

የጎዴ አጠቃላይ ሆስፒታል የምግብ እጥረት ህክምና መስጫ ማዕከልን፣ ፈጣን ምላሽ ህክምና አሰጣጥን እንዲሁም በጎዴ ወረዳ የክትባት፣ የስነ ምግብ፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ድጋፍ፣ የእንስሳት ምገባ ድጋፍ አገልግሎት ለማህበረሰቡ በፌደራል በክልልና በአጋር ድርጅቶች ቅንጅት እየተሰጠ የሚገኝበትን ሁኔታም ተመልክቷል።


ከጉብኝቱ በተጨማሪም ቡድኑ ከክልሉ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሙስጤፌ መሃመድ እና ከሌሎች የክልሉ ሃላፊዎች ጋር በድርቅ የተጎዱ ቦታዎችን ምላሽ አሰጣጥና ድጋፍ ዙሪያ ውይይት አድርጓል።