የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በደቡብ ወሎ ኮምቦልቻ ከተማ በመገኘት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ዜጎች የሚያገኙትን የጤና አገልግሎት በተመለከተ ምልከታ አካሄዱ
በጥፋት ሀይሎች ለተጎዱ የጤና ተቋማትና በችግሩ የተፈናቀሉ ዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጻል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እና የሚኒስቴሩ የእናቶች እና ህጻናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም ከኮንቦልቻ ከተማ ከንቲባ እና ከጤና መምሪያ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን በመጠለያ የሚገኙ ዜጎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅትም ከዩኤንኤፍፒኤ (UNFPA) በድጋፍ የተገኙ 590ሺ ዶላር ግምት ያላቸው የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን፣ የስነ ተዋልዶ ኪቶችን፣ የኮቪድ መከላከያ ግብዓቶች የተረከቡ ሲሆን በርክክቡ ወቅትም ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንደተናገሩት የጥፋት ሀይሎች በጤና ተቋማት ያደረሱትን ውድመት እና ዝርፍያ እንደዚሁም የበርካታ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን በዚህም ለተለያዩ የጤና ጉዳቶች መጋለጠቸውን ጠቅስው በዩኤንኤፍፒኤ (UNFPA) በኩል የተደረገው ድጋፍ በአስፈላጊ ወቅት እና አካባቢ መደረጉንም ገልጸዋል።