ጠንካራ የፋይናንስና ፍትሃዊ የጤና ስርዓቶች ጥራት ላለው የጤና አገልግሎት
በጅግጅጋ በሚካሄደው የጤናው ዘርፍ ልማት ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎ ተሳታፊዎች በተለያዩ ጤና ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት አካሂደዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ እና የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰሃረላ አብዱላሂ የተገኙበት የፓናል ውይይት የጤና ፋይናንስን እና ፍትሃዊነትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡
የጤና ፋይናንስ ስርዓቱን አስመልክቶ በቀረበው ፓናል ውይይት ከሃገር አቀፍና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሃብት ማሰባሰብ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን መንግስት ከጠቅላላው በጀት ውስጥ 13 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆነውን ለጤናው ዘርፍ እንዲመደብ ለማድረግ ተችሏል፡፡
የግሉን የጤና ዘርፍና የመንግስትን ትብብር ለማጠናከር በተሰራው ስራ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በተለይም የጤና ግብአቶች ምርትና ተርሸሪ ኬር ላይ እንዲጨምር ማድረግ መቻሉ በውይይቱ ተነስቷል፡፡