ከግሎባል ፈንድ በተገኘ 453 ሚልዮን የአሜርካ ዶላር ድጋፍ የቲቢ፣ የኤች አይ ቪ፣ የወባ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም የጤና ስርአትን በማጠናከር ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች ናቸው።
ፕሮጀክቶች የተከናወኑት አገራችን በተለያዩ ችግሮች ማለትም ኮቪድ 19፣ የተለያዩ ግጭቶች እና ድርቅ ውስጥ በነበርችበት ጊዜ ቢሆንም፣ ፈንዱን በመጠቀም አበረታች ውጤቶችን ለማስመዝገብ ተችላል። የተገኙ ውጤቶችን ለማስፋፋትና ያጋጠሙ ችግሮችን በዘላቅነት ለመፍታት የሚያስችል አውደ ጥናት ተካሂዷል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የጤና ሚኒስቴር፣ የክልል ጤና ቢሮና የኤጀንሲ ኃላፊዎች፣ የድጋፍ ባለሙያዎች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፣ ግሎባል ፈንድ የኢትዮጵያ መንግስት የጤናውን ስርዓት በማጠናከር በተለይም የኤች አይ ቪ፣ የወባ እና የቲቢ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚተገበሩ ስራዎች ላይ ለሚያከናውናቸው የድጋፍ ተግባራት እና ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡