የአፍሪካ ህብረት ልማት ኤጀንሲ-ኔፓድ የሚኒስትሮች መድረክ  ለተዋልዶ ጤና ትኩረት በመስጠት ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማፋጠን እና የአፍሪካን ስነ-ህዝብ አቅም መጠቀም” በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል፡፡ 

  • Time to read less than 1 minute
Dr Mekdes Daba

በመድረኩ  የተሳተፉ የአፍሪካ ሃገራት ሚኒስትሮች ልምድ የሚለዋወጡበት እና በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን መግባባት ላይ የሚደርሱበት መድረክ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በመድረኩ የመክፈቻ ንግግራቸው ያስረዱ ሲሆን፤ ጉባኤው በዋናነት የስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረቱን ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ 


ኢትዮጵያ በስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ማፍሰሷን ያስታወሱት ዶ/ር መቅደስ፤ በዚህም የእናቶች እና ህጻናት ህልፈትን መቀነስ መቻሉን እና አጠቃላይ የጤና ስርአትንም ማሻሻል መቻሉን አብራርተዋል፡፡ የአፍሪካ ሃገራት የሃገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ አፍሪካ በጤና ዘርፍ እራሷን እንድትችል መስራት ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ያጋጠሙ የፋይናንስ ክፍተቶችን የሃገር ውስጥ ሃብትን በማሳባሰብ እና ከአጋሮች ጋር በትብብር በመስራት መቅረፍ እንደሚገባ አክለዋል፡፡

 
ያለ ተዋልዶ ጤና ዘላቂ ልማትን ማምጣት እንደማይቻል የተናገሩት ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ልማት ኤጀንሲ-ኔፓድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ናርዶስ በቀለ-ቶማስ ሲሆኑ፤ የአፍሪካ ሃገራት ለቤተሰብ ምጣኔ የሚመድቡትን በጀት ማሳደግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ የስነ-ተዋልዶ ጤና ያጋጠሙ ተጋዳሮቶችን በመግለጽ የመፍትሄ አቅጣጫም አስቀምጠዋል፡፡ 


በመድረኩ 24 ቅድሚያ የሚሰጣቸው መድሃኒቶችን በአፍሪካ ለማምረት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በአውዳ-ኔፓድ እና ቻይ የተፈረመ ሲሆን፤ የአውዳ-ኔፓድ አመታዊ ሪፖርት ቀርቦ በመድረኩ ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡