ኦንኮሳርኪያሲስ የቆዳና የአይን ችግር የሚያስከትል በሽታ ነው። በሽታው ኦንኮሰርካ ቮልቮሉስ በሚባል ኢንፌክሽን ምክንያት የሚከሰት ሲሆን፤ ምልክቶቹም ከባድ የማሳከክ ስሜት፣ ከቆዳ ስር ያሉ እብጠቶች እና ዓይነ ስውርነት ናቸው። እንደ DEET ያሉ ነፍሳትን የሚከላከሉ መድኃኒቶችን መርጨት እና ረጅም እጅጌ ያላቸውን ሸሚዞች እና ሱሪዎችን በመልበስ በሽታውን መከላከል ይቻላል።
በአመታዊ ጉባኤው በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንደተናገሩት፤ ኮሚቴው እያደረገ የሚገኘው ኢንቨስትመንት በሽታውን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት እያፋጠነ ይገኛል፡፡ ጤና ሚኒስቴር በሽታው በስፋት በሚገኝባቸው አካባቢዎች የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በመጨመር የመከላከል እና አክሞ የማዳን ስራዎችን በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከየልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር በመስራት ኦንኮሳርኪያሲስ ከኢትዮጵያ እንዲጠፋ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ዶ/ር ደረጀ፤ በተለይም በኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ድንበር የበሽታ ቁጥጥርን ለማሳደግ አጋሮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የዘንድሮው ጉባኤ መሪ ቃል “ኦንኮሳርኪያሲስን ለማጥፋት የአጋርነትን ማጠናከር” በሚል መከበሩ በትብብር የመስራትን አስፈላጊነት ያረጋገጠ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ህይወት ሰለሞን የገለጹ ሲሆን፤ በሽታውን ለማጥፋት ከጎረቤት ሃገሮች ጋርም በትብብር እየተሰራ መሆኑን አክለዋል፡፡
- 2 views