የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎትን ፍትሃዊና ተደራሽን ለማጠናከር የሚያግዙ የተሟላ የህክምና ቁሳቁስ ያላቸው 10 ተንቀሳቃሽ የህክምና ክሊኒኮችን ለመለገስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት ተፈራርሟል
በጃፓን መንግስት በኩል ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታኮኮ ባስተላለፉት መልዕክት በሀገራቸው የተደረገው የ500 ሚሊዮን የጃፓን የን/3.5 ሚሊዮን ዶላር/ ድጋፍ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ክልሎች ድጋፍ የሚሹ ተብለው በተለዩት በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላና በደቡብ ምዕራብ ክልሎች ያለውን የእናቶችና ህፃናት ጤና በማሻሻል የሚሞቱ እናቶችና ህፃናትን ቁጥር እንደሚቀንስ ያላቸውን ተስፋ ጠቁመው ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮቹ አልትራሳውንድና ኤሌክትሮ ካርዲዮግራፍን ጨምሮ መሰረታዊ የህክምና ቁሳቁሶችን ያሟሉ እንደሚሆኑ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያና ጃፓን ከ1970ዎቹ ጀምሮ የኢኮኖሚ አጋርነታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን የገለፁት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሪት ሰመሬታ ሰዋሰው በተለይም በመሰረተ ልማት፣ በግብርና ምርታማነት፣ በሰው ሀብት ልማትና በግሉ ዘርፍ እድገት ዙሪያ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆናቸውን አውስተው ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የእናቶችንና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ በቁርጠኝነት እየሰራች ቢሆንም ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ለማድረግ ብዙ ይቀራል ብለዋል፡፡ ለዚህም ድጋፉ አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑን ጠቁመው የጃፓንን ህዝብና መንግስት አመስግነዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ጤና ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተሰራው ስራ የእናቶችና ህፃናት ጤና መሻሻሉን ጠቁመው ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ጤና ተቋማትን ከማሳደግ ባሻገር የተለያዩ ስትራቴጅዎች እየተተገበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም ጤና ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት አመታት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በድርቅና በግጭት ምክንያት ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች የጤና አገልግሎት እንዳይቋረጥ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ የጤና ባለሙያዎችን ያካተቱ ተንቀሳቃሽ ቡድኖች በመላክ አገልግሎቱን ሲሰጥ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የጃፓን መንግስትም የስትራቴጅ ዕቅዳችን የሆነውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ፍትሃዊነት አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ ለሆኑ አካባቢዎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ 10 ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮችን በመለገሳቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ድጋፉ ለነብሰጡርና ለሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም ለህፃናት አገልግሎት እንደሚውልም አረጋግጠዋል፡፡