የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ተጀመረ

  • Time to read less than 1 minute
Breast cancer

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በፈረንጆች ጥቅምት ወር የሚደረገው የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በፓዮኒር ምርመራ ማዕከል ከመስከረም 20 ጀምሮ ለአንድ ወር በነፃና በግማሽ ክፍያ በሚሰጥ ምርመራ ተጀምሯል።


በየዓመቱ 40 ሺህ ያህል ሰዎች በጡት ካንሰር ምክንያት እንደሚሞቱ የጠቆሙት በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት ዘላለም ካንሰር ስር ከሰደደ በኋላ ለማከም የሚያደርሰውን የጤና፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስና ለመከላከል ቀድሞ በመመርመር የጤናን ሁኔታ ማወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።


በጤና ሚኒስቴር ካንሰርን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ያብራሩት ዳይሬክተሯ የማህፀን ጫፍ ካንሰርን ለመከላከል 14 አመት ለሞላቸው ልጃገረዶች የሚሰጠውን የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ጨምሮ የቅድመ ካንሰር ምርመራና ህክምናን በተመለከተ የተሠሩ ስራዎችን አብራርተዋል። የጡት ካንሰርን በተመለከተም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል። 


መከላከልን መሰረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ በመደገፍ እንዲሁም ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት ፓዮኒር እያደረገ ላለው ጥረት አመስግነው ሌሎች ተቋማት አርአያነቱን እንዲከተሉ፤ እናቶችና እህቶችም ዕድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አድርገዋል።


በጥቁር አንበሳ የካንሰር ህክምና ክፍል ሃላፊ ዶክተር ኤዶም ሰይፈ በበኩላቸው ምርመራው መጀመሩ ስጋት እያላቸው የት እንደሚሄዱ ባለማወቅ ወይም አመች ሁኔታ ባለማግኘት አገልግሎቱን ያላገኙ እናቶችና እህቶች እንደሚያነቃቃ ጠቅሰው ከምርመራ በኋላ በሽታው ቢገኝባቸው ከጥቁር አንበሳ ጋር በጥምረት እየሰራ ወደሚገኘው ቸርችል ጤና ጣቢያ በመሄድ ህክምናውን ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።


የፓዮኒር ምርመራ ማዕከል መስራችና ባለቤት አቶ ብሩክ ፈቃዱ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ንቅናቄ ማድረጋቸውን አስታውሰው በማዕከላቸው ዓለም የደረሰበት ዘመናዊ 3ዲ ማሞ ግራፊ አልትራሳውንድና ኤም አር አይ ማሽኖች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።


ነገር ግን ብዙ ባለሙያው እና ዘመናዊ ማሽን መግዛት ብቻ ሳይሆን ግንዛቤን ማዳበርም አስፈላጊ በመሆኑ ለተመረጡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በነፃ በማዕከሉ ለምርመራ ለሚመጡ ደግሞ በግማሽ ክፍያ ከመስከረም 20 ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል
በፓዮኒር ለአንድ ወር በሚቆየው የጡት ምርመራ የግማሽ ክፍያ ቅናሽ ለመጠቀም የሚፈልጉ ቦሌ አለም ህንፃ ስር በሚገኘው ዋና ቅርንጫፍ በመገኘት ወይም በስልክ ቁጥር 0908656565/ 0908646464 እና 0912039939 መደወል እንደሚችሉ ተገልጿል።