የጤና ሚኒስቴር ከደብረብርሀን ዩንቨርሲቲ፣ ከስማይል ትሬን (Smile Train) እና ከኬፕ ታውን ዩንቨርሲቲና ጋር በመቀናጀት ለ3 ቀናት በአዲስ አበባ ሲያካሂድ የነበረውን የዓለም የቀዶ ህክምና፣ የድገተኛና ፅኑ ህሙማን ህክምና አገልግሎት የአመራር ክህሎት ዓውደ ርዕይ ተጠናቋል፡፡
በጥናታዊ ዓውደ ርዕዩ የማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ እንደተናገሩት አውደ ርዕዩ በዓለም አቀፍ የቀዶ ሕክምናና የድንገተኛና ጸኑ ህክምና ላይ ትኩረት አድርጎ መወያየቱ የሚደገፍና ትክክለኛው ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው እንደ ሃገር የአገልግሎቱን ጥራትና ተደራሽነት ለማስፋፋት የጤና ሚኒስቴር በ5 ዓመቱ እስራቴጂክ ዕቅድ አካቶ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ የቀዶ ህክምና፣ የድገተኛና የፅኑ ህሙማን ህክምና አገልግሎት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ያለው አፈፃፀም አሁንም ዝቅተኛ እንደሆነ ጠቅሰው በቀጣይ አገልግሎቱን በማሻሻልና ቀልጣፋ እንዲሆን በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ የገልጹት ሚነስትር ደኤታው በዚህም የታካሚዎችን እንግልት መቅረፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ አክለውም የጤና አገልግሎቱን ስታንዳርዱን የጠበቀ እንዲሆን የግል ጤና ዘርፉንና ዩንቨርሲቲዎችን ባማከለ መልኩ (public private partnership) የጤና ስርዓቱን ማሻሻልና የጤና ዘርፋንም አመራር ማዘመን እንደሚገባ አሳስበው ተሳታፊዎች በዓውደ ጥናቱ ያገኙትን ግንዛቤና ልምድ የሚሰሩባቸውን ጤና ተቋማት አገልግሎት ለማሻሻል እንዲረባረቡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በጥናታዊ ዓውደ ርዕዩ የጤና ሚኒስቴር የፕሮግራም ዘርፍ ሀላፊዎች፣ የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን የስራ ሀላፊዎች፣ የሆስፒታል ስራ አስኪያጆች፣ በዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ማዕከል ባለሙያዎች እንዲሁም የተለያዩ አጋር ድርጅት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን የ5 ዓመት የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን ዕቅድ፣ የዓለም አቀፍ የቀዶ ህክምና አገልግሎትና የአመራር ክህሎት እንዲሁም የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።