የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ተደራሽነትና ሽፋንን አስመልክቶ በጤና ሚኒስቴር በየደረጃው የሚገኙ ኃላፊዎች፣የጋቪ፣ የዩኒሲኤፍ እና የአለም ጤና ድርጅት ተወካዮችና ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተደረጓል፡፡
ባለፉ በርካታ ዓመታት የክትባት አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በቁርጠንነት ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ አጋር ድርጅቶችን በማመስገን ንግግራችውን የጀመሩት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ሲሆኑ በተለይ የኮቪድ ወረርሽኝን ከመግታትና አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት ረገድ ባለድርሻ አካላት የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡
እንደሀገር ከነበርንበት 4% የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ሽፋን አሁን ላይ ለደረስንበት ከ20% በላይ ለሚሆነው የክትባት አፈፃጽም በዋነኛነት የበላይ አመራሩ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ተሳትፎ አንዱ ምክንያት እንደሆነ የገለጹት ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው በተለይ የማይበገር የጤና ስርዓት ከመፍጠር ረገድ የአጋር አካላት ተሳትፎ የማይተካ እንደነበር ገልጸው ወደፊትም ይህንንም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ክቡር ዶ/ር ደርጄ ዱጉማ አክለውም የኮቪድ - 19 መከላከያ ክትባትን በመደበኛ የጤና አገልግሎት ውስጥ በማቀናጀትና በማካተት ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው ይህም ወደ ህክምና ማዕከል የሚመጡ የተለያዩ ተገልጋዮችን በተቀናጀ አግባብ ተጠቃሚና ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ መጀመሪያ ከነበረበት አሁን ለደረሰበት የኮሮና መከላከያ ክትባት ሽፋን ተደራሽነት መጨመር እንዲሁም ለተመዘገበው እጅግ አመርቂ ውጤት ላቅ ያለ ምስጋናቸውን ያቀረቡት በኢትዮጵያ የክትባት ተድራሽነት ላይ በስፋት እየተንቀሳቀስ የሚገኘው የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት አቅርቦት ጥምረት ኃላፊ ሚስተር ቴድ ቺያባም ናቸው።
ኃላፊው አክለውም እንደ ሀገር የተቀመጠውን ግብ ለመድረስ የክትባት ተዳራሽነት ላይ በዕድሜ የገፉ አረጋውያን ዜጎችንና ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን የህበረተሰብ ክፍሎች ትኩረት ሰጥቶ መስራት፣ ክትባቱ ማህበረሰቡ በቅርበት ሊያገኘው በሚችል አግባብ በመኖሪያ አከባቢው ተደራሽ እንዲሆን እና በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ታሳቢ በማድረግ መስራት እንዳለበት ኃላፊው ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱም በድርቅና በግጭት ለተጎዱ አካላት እንዲሁም ተደራሽ ባለሆኑ አከባቢዎች ለሚገኙ ዜጎች አስፈለጊውን በጀት በመመደብና ትኩረት በመስጠት በተቀናጀ አግባብ እንደሚሰራ ተገልጿል።