ድጋፉን ያደረገው የኮካ ኮላ ኩባንያ የአለም በጎ አድራጎት ክንፍ የሆነው ኮካ ኮላ ፋውንዴሽን ነው፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይፋዊ የርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የተደረገው ድጋፍ የቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለታካሚዎች የጤና አገልግሎት ለመስጠት ያለውን አቅም ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ከ286 ሺህ ዶላር በላይ ወጪ የሚያወጡት ቁሶቹ፣ የግል የጤና ደህንነት መሳሪያዎች፣ የጽንስ እና ማህጸን ህክምና መሳሪያዎች፣ የህጻናት ህክምና ቁሳቁሶች፣ እና የባዮ ሚዲካል መሳሪየዎችን ያካተቱ ሲሆን ይህም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብሎም በሪፈራል የሚመጡ ማህበረሰብ ክፍሎችን ለማገልገል የሚውል ነው፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ፕሮቮስት ዶ/ር ወንድማገኝ ገዛኸኝ ከኮካ ኮላ ፋውንዴሽን የተገኘው ድጋፍ፣ ተቋሙ እያደረገ ላለው የህክምና፣ የጤና እንክብካቤ እና ሌሎች ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ከመላው ኢትዮጵያ ለሚመጡ ህሙማን ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል፡፡
የኮካ ኮላ ቤቨሬጅስ አፍሪካ-ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳሬል ዊንሰን በበኩላቸው እንዳሉት ድጋፉ ሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እየሰራ ያላውን ተግባራት አቅም የሚያጠናክር እና የአገልግሎት ጥራቱን ከፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ የኮካ ኮላ ቤቨሬጅስ አፍሪካ-ኢትዮጵያ አመራሮች እና የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አስተዳደር ሰራተኞች ተግኝተዋል፡፡