ሰማሪታንስ ፐርስ ኢንተርናሽናል ሪልፍ የእርዳታ ድርጅት ለኢትዮጵያ 12.5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስና ግብአት ድጋፍ አደረገ

  • Time to read less than 1 minute
Samaritan’s Purse

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በቦሌ አየር ማረፊያ ተገኝተው ከሰማሪታንስ ፐርስ ኢንተርናሽናል ሪልፍ ካንትሪ ዳይሬክተር ሪል ላን ድጋፉን ተረክበዋል፡፡ ዶ/ር ሊያ በርክክብ ስነስርዓቱ ጊዜ እንደተናገሩት መቀመጫውን በአሜሪካ አገር ያደረገው የሰማሪታንስ ፐርስ ኢንተርናሽናል ሪልፍ በኢትዮጵያ ከንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን፣ ከኮቪድ-19 እና በሌሎች የድንገተኛ ምላሽ ድጋፍ ስራዎችን ሲሰራ የቆየ ተቋም መሆኑን አንስተው አሁን 12.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የህክምና ግብአትና መሳሪያዎች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ 


ድጋፉም በአጠቃላይ እየተደረገ ላለው የመልሶ ማቋቋም ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተናገሩ ዶ/ር ሊያ የህክምና ቁሳቁስና ግብአት ድጋፉን በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ የጤና ተቋማት መልሶ ማቋቋሚያ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡ ይህም ድገፉን መስጠት ብቻ ሳይሆን በቴክኒሻኖቻቸው አማካኝነት አገልግሎቱን ማስጀር የሚደረስ እገዛ እንደሚደረጉም አክለው የገለጹ ሲሆን ተቋሙ እያደረገ ላለው ድጋፍ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። 


የሰማሪታንስ ፐርስ ኢንተርናሽናል ሪልፍ ካንትሪ ዳይሬክተር ሪል ላን ድጋፉ በጦርነቱ ለተጎዱ ዜጎች የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለመደገፍ እንዲውል ታስቦ የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። በግጭቱ የተጎዶ ዜጎችን ለመርዳት በመቻላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናገሩ ዳይሬክተሩ  ድጋፉ ተጠናክሮ እንሚቀጥል ገልጸዋል፡፡  


በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የጤና እና ጤና ነክ ግብአት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ሰንታየሁ በበኩላቸው በክልሉ በጦረነቱ ምክንያት የወደሙ የጤና ተቋማትን በዝርዝር ከቀረቡ በኋላ ይህን ውድመት ተረድቶ ድጋፍ ላደረጉ ሰማሪታንስ ፐርስ ኢንተርናሽናል ሪልፍ የእርዳታ ድርጅት እና ሌሎች ድርጅቶች የአማራ ክልል የጤና ቢሮን በመወከል ምስጋና አቅርበዋል፡፡