ይህ የቤተሰብ እቅድ 2030 የቃል መግቢያ ሰነድ አለም አቀፋዊ ሲሆን 69 ሀገራት የሚሳተፉበት ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት በ2030እ.ኤ.አ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን በሀገርአቀፍ ደረጃ ለማሳካት በምንገባው ቃል መሰረት የእናቶችና የህፃናትን ጤና ብሎም የአፍላ ወጣቶችንና የወጣቶችን ስነ-ተዋልዶ ጤና በማሻሻል የተሻለ ጤናማ ዜጋ በመፍጠሩ ረገድ መንግስት ሰፊ ስራ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል:: የሁሉንም ተሳትፎ ባካተተ መልኩ የተዘጋጁት የጤናዉ ፖሊሲ ስትራቴጂዎችና የማስፈጸሚያ ሰነዶችን ወደ ተግባር የመለወጥ ስራ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያሰፈልግና በገባነው ስምምነት መሠረት ያሉብንን ተደራራቢ ጫናዎችን በመቋቋም ብሎም በጋራ በጥምረት በመስራት ጤናማ ትውልድን ለመፍጠር እና ጤናማ ሀገርን ለመገንባት ይህ የቃል መግቢያ ሰነድ መዘጋጀቱንና ይፋ መደረጉን ተናግረዋል::
በየአመቱ የሚመዘገበው የእናቶች ሞት በፊት ከነበረው በከፍተኛ ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን የስራችን ውጤት ቢያሳይም አሁንም ከ 100 ሺህ እናቶች ዉስጥ 401 የሚሆኑ እናቶች ከወሊድ እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ እንደሚሞቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልፀዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር መሰረት ዘላለም እንዳሉት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የእናቶችና ሕፃናት ጤና ለማሻሻል እንዲሁም የሴቶችንና ሕፃናትን ህይወት ለመታደግ ዋነኛ መፍትሄ መሆኑንና የእናቶችና የሴቶችን ሞት ለመቀነስ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን በተጠናከረ መልኩ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ምርጫን መሠረት ባደረገ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰነዱ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የክልል ጤና ቢሮ ተወካዮች ፣የአጋር ድርጅቶችና የሙያ ማህበራት ተወካዮች እንድሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።