በድጋፍ ርክክቡ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንደተናገሩት አሁን ላይ አገራችን እና ህዝቦቿ ከመቼውም በተለየ ከውስጥም ከውጪም ፈተናዎች እና መሰናክሎች የገጠሟት ወቅት ላይ እንደምንገኝ ገልጸው በሁሉም መስኮች በማህበራዊ ፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በውጭ ጉዳዮቻን ላይ የገጠሙን ችግሮች ለጊዜው ሊፈትኑን እና ሊከብዱን ቢችሉም እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ እነዚህ ዓይነት መሰል ውስብስብና ከባድ ችግሮች ሲገጥሙን ይህ የመጀመርያችን አይደለም፤ ቀደም ሲል ከውስጥም ከውጭም ችግሮች የገጠሙን ወቅት በነበረን አገራዊና ህዝባዊ ፍቅር፣ በነበረን መደማመጥና መግባባት፣ ሚሊዮኖች እንደ አንድ ሆነን፣ አንዱ እንደሚሊዮን ሆኖ ችግሮቹን እና ፈተናዎችን ተሻግረን ዛሬ ላይ መድረሳችን በቂ ማሳያ ነው ሲሉ የአንድነት ጥንካሬያችንን አስታውሰዋል::
አሁንም የተከፈተብን ሁሉን ዓይነት ዘመቻና አገር የመበታተን አደጋ መመከትና ማስቀረት የምንችለው ብቸኛውና ትክክለኛው አማራጭ እንደ ቀደመው ታሪካችን የውስጥ አንድነታችንን እና ጥካሬያችንን፣ ነባር የመደጋገፍና የመተሳሰብ እሴቶቻችንን በማጠናከርና በብዙ ክንዳችን ስንተባበር ብቻ እንደሆነም ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ በዚህ አገርን የማዳን ዘመቻ ፣ በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎቻንን የመደገፍና የማቋቋም ስራ ፣ ከመከላከያ ጎን በደጀንነት የመቆሙ ጉዳይ ለጥቂቶች ሰጥተን የምንተወው ተግባር እንዳልሆነ ገልጸው እያንዳንዱ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ያለአንዳች ማመንታት በሙሉ ልብና በአንድነት ሊያደርገው የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል ዶ/ር ሊያ፡፡
አገራችን የገጠማትን ፈተና ህይወቱን ሳይሰስት በግንባር የሚፋለመውን የአገራችንን መከላከያ ሰራዊት መደገፍና ማጠናከር፣ ለመከላከያችን ያለንን አብሮነትና ደጀንነት ባለን አቅምና በምችለው ሁሉ በተግባር ማሳየትና ዘመቻው በአጠረ ጊዜ በድል እንዲጠናቀቅ ማስቻል ከሁሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በቀዳሚነት እንደሚጠበቅም ዶ/ር ሊያ የትብብር አስፈላጊነትን ተናግረዋል::
በዚህም መሠረት በጦርነቱ ጉዳት ለሚደርስባቸው የመከላከያ ሠራዊት፣ ፀጥታ ሀይላት እና ዜጎች አስፈላጊው ህክምና እንዲያገኙ ከመከላከያ ሚ/ር የክልል ቢሮዎች ጋር በመሆን በተለያዩ ጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲያገኙ የመድሃኒት፣ የግብአት፣ የሰው ሃይል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንና በተጨማሪም በግጭቱ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም የጤና ሚኒስቴር ስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር እየተዋደቀ ለሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከዚህ ቀደም ቃል በገባነው መሰረት ከወር ደመወዛችን የሚደረገው መዋጮ አጠናክረን የቀጠልን ሲሆን በተጨማሪም ከመቼውም በላይ የሚስፈልገውን የደም ፍላጎት ለሟሟላት የሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ሰራተኞች በተለያዩ ዙሮች ደም መለገሳቸውን አስታውሰው ድጋፋችንን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል ብለዋል።
አሁንም አሉ ዶ/ር ሊያ ቀን ከሌሊት እየተዋደቀ ላለው ለጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት አለኝታነታችንን በተግባር ለመግለፅ በተለያዩ ዙሮች ካደረገው የገንዘብ፣ የአይነትና የደም ድጋፍ በተጨማሪ ዛሬ ለመከላከያ ሰራዊታችን ካለን በጀት የተወሰኑ ስራዎችን በማጠፍ 30 ሚሊየን ብር በገንዘብ እና 1.5 ሚልየን ብር የሚገመቱ የተለያዩ የዓይነት ድጋፎችን የጤና ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን በማሰባሰብ ለመከላከያ ሚንስቴር የምናስረክብ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
ስንተባበር ድላችን ቅርብ ነው፣ ስንተጋገዝ ችግራችን ቀላል ነው፣ ስንደማመጥ ድምጻችን ጉልህ ነውና አሁን ላይ ያለንበት ወቅትና የገጠመን የውስጥና የውጭ ፈተና እኛን ከመቼውም በላይ እንድንተሳሰብና እንድንደጋገፍ ፣ አቅማችንን እንድናጠናክርና ክንዳችንን እንድናስተባብር ፣ ወኔያችንንም ከፍ እንድናደረግ የሚጠይቅ ጊዜ በመሆኑ ጤና ሚኒስቴር በሚችለው አቅም ሁሉ ለአገር መከላከያ ሰራዊታችን የምናደረገውን ድጋፍ አጠናክረን እንደምንቀጥልና አብረናችሁ እንደሆንን እንገልጻለን ሲሉ ዶ/ር ሊያ ለሀገር መከላከያ ያላቸውን ደጀንነት እንደሚኒስቴር መስርያ ቤት አረጋግጠዋል።
የተደረገውን ድጋፍ የተረከቡት የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴአታ ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ ኢትዮጵያዊነት የማይበጠስ ጠንካራ ገመድ መሆኑን በመግለጽ ጤና ሚኒስቴር ብዙ ስራ ሸፍኖ ከመስራት ጎን ለጎን ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፤ ድጋፉ እስከመጨረሻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋም ገልፀዋል፡፡