ከፖሊዮ ነጻ የሆነ አለም እንፍጠር በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ በሲዳማ ክልል በአዋሳ ከተማ እና በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን ዲላ ከተማ የክትባት ዘመቻ መርሀግብር ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በመርሀግብሩ እንደተናገሩት የጤና ሚኒስቴር ፖሊዮን ለማጥፋት በመደበኛ ክትባትና በዘመቻ በሚሰጥ ክትባት ከሀገራችን ለማጥፋት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
ባለፉት አመታትም በተከናወነው ስራ ፖሊዮን ማጥፋት ተችሎ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አከባቢዎች እየታየ ያለውን የልጅነት ልምሻ በሽታ ለማጥፋትም እስከ ጤና ኬላ በተዘረጋ መዋቅር እና ከአጋር አካላት ጋር በተቀናጀ አሰራር እየተተገበረ መሆኑን ተናግረው ይህም መንግስት ለሕጻናት ጤና መሻሻል ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፖሊዮን በሽታ ጨርሶ ለማጥፋት እየተከናወኑ ከሚገኙት ስልቶች ውስጥ መደበኛ የክትበት አገልግሎትን ማጠናከር፣ ሕጻናትን የፖሊዮ በሽታ የመከላከል አቅም ለማዳበር ተጨማሪ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻዎችን አስፈላጊነት የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው የፖሊዮ በሽታ ቅኝትን ማጠናከር እና ከአጎራባች አገሮች ጋር ያለውን የክትባት አገልግሎት ማጠናከር ዋና ዋናዎቹ ተግባራት መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
በየዓመቱ ጥቅምት 12 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የፖሊዮ ቀንም በፖሊዮ ማጥፋት ተግባራት ላይ የምንሰራቸውን ሥራዎች አጠናክረን የምንሰራበት እና ተጨማሪ ቁርጠኝነት የምንገባበት ይሆናል ሲሉም ህብረተሰቡ ከአምስት አመት በታች ያሉ ልጆቹን እንዲያስከትብ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በዘመቻው መርሀግብርም በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን ዲላ ከተማ ጤና ጣቢያ እና በሲዳማ ክልል በሀዋሳ ከተማ ሆስፒታል እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህጻናት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት በመስጠት በይፋ ያስጀምሩ ሲሆን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፣ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ፣ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ፣ የአለም ጤና ድርጅት፣ የሮተሪ ኢንተርናሽናል፣ የዩኒሴፍ እና ኮር ቲም አመራሮች ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የፖሊዮ ቫይረስ ተጎጂ ሁለት ግለሰቦችም የህይወት ልምዳቸውን አካፍለዋል ፡፡