ጤና ሚኒስቴር በጤና ተቋማት የሚሰጡ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል የማህበረሰብ አስተያየት መመዘኛ ካርድ (community Score Card) እየተገበረ ሲሆን በዚህ የአተገባበር ስርዓት ዙርያ ኢትዮጵያ ያላትን አሰራርና ልምድ ለማካፈል ብሎም በጋና ሀገር ያለውን የማህበረሰብ አስተያየት መመዘኛ ስርዓት ትግበራ ተሞክሮ ለመቅሰም ከተለያዩ የስራ ክፍሎችና ክልሎች የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ቡድን በጋና ሀገር ልምድ ልዉዉጥ እያደረገ ይገኛል።
በዚህ የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብር ላይ የጋና ጤና ሚኒስቴር አጠቃላይ የጤና ስርዓቱ ምን እንደሚመስል እና የአተገባበር ደረጃዎችን የተመለከተ በጋና ሚኒስቴር መ/ቤት ተወካዮች ገለጻ የተደረገ ሲሆን በተለይም የማህበረሰብ አስተያየት መመዘኛ ካርድ (ስኮር ካርድ) የአገልግሎት ጥራት ማሻሻል፣ የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት የማግኘት ፍላጎት እና ተሳትፎ መጨመር እንዲሁም ዜጎች በጤና ተቋማት ላይ እያሳደሩት ያለውን አዎንታዊ እምነት መገንባት ላይ ያለዉን አስተዋጽኦ ገለጻ ተደርጓል።
ቡድኑ በቀጣይ በጋና የማህበረሰብ አስተያየት መመዘኛ ካርድ (ስኮር ካርድ) ስርአት ትግበራ ምን እንደሚመስል እና በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያመጣውን መሻሻል በተጨባጭ ለመመልከት በተቋማት እና በማህበረሰብ ደረጃ ምልከታ የሚያካሂድ ሲሆን በኢትዮጵያም እየተተገበረ የሚገኘውን የማህበረሰብ አስተያየት መመዘኛ ካርድ (ስኮር ካርድ) አስመልክቶ ያላትን ልምድና የተገኘዉን ውጤት በተሞክሮነት ያጋራል።