በብራዛቪል ኮንጎ እየተካሄደ ያለዉ 74ኛው የአፍሪካ አህጉር የአለም ጤና ድርጅት መድረክ ቀጥሏል።
በመድረኩ በአፍሪካ በተለያዩ ግዜያት ወረርሽኞችና ሌሎች ድንገተኛ የጤና አደጋዎች እየተከሰቱ የማህበረሰቡ ጤና ስጋት መሆናቸዉ አሳሳቢ መሆኑ ተገልጿል።
ኢቦላ፣ ኮቪድ 19 እና ሌሎች ወረርሽኞች በአፍርካ ቀጠና ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን በማስታወስ አሁን ላይ ኤም ፖክስ (Mpox) የደቀነዉ የጤና አደጋ በተለይ ለአፍሪካ አሳሳቢ መሆኑ ተንስተዋል።
በመደረኩ ላይ በመገኘት ሀሳባቸዉን ያቀረቡት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በኤም ፖክስ (Mpox) የተጠረጠረም ሆነ የተያዘ ሰዉ አለመኖሩን ጠቅሰዉ በሽታዉ እንዳይከሰት፣ ከተከሰተም ለመቆጣጠር የሚያስችል ሰፊ የቅደመ መከላከልና ቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍርካ የሚከሰቱ ወረርሽኞችንና ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር “ለአፍርካ ችግር የአፍርካ መፍትሄ” በሚል መርህ አገራት በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል ሚኒስትሯ።
የአፍሪካ መሪዎች በጉዳዩ ላይ በመምከር የተለያዩ መፍትሄዎችን መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር መቅደስ የራስን የአመራር አቅም ማጎልበት፣ የጋራ ተቋማትን ማጠናከር፣ ሀብት ማፈላለግ፣ በድንበር አከባቢ የሚደረጉ የቅኝትና ቁጥጥር ሰራዎችን በትብብር ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የመካከለኛ ዘመን የጤና ኢንቨስትመንትና ስትራቴጂክ እቅድ አዉጥታ እየተገበረች መሆኑን ያነሱት ዶ/ር መቅደስ ወርሽኞችንም ሆነ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በዘርፉ የሚደረግ ኢንቨስትመንትን መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
የጤናዉ ዘርፍ የአመራር ክህሎትና የጤና ባለሙያዉ አቅም ማሳደግ ልዩ ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ከሚመለከተዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በዚህ ረገድ የሚታደርገዉን ትብብርና ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ፓሊዮን ለማስወገድ በኢትዮጵ እየተሰራ ያለዉን ተሞክሮም በመድረኩ አቅርበዋል። የፓሊዮ ክትባት በመደበኛዉ የክትባት ፕሮግራምና በዘመቻ መልክ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዉ ከጎረቤት አገሮች ጋር መግቢያና መዉጫ በሮች እንዲሁም በአየር መንገድ ላይ በስታንደርዱ መሰረት የቅኝትና ቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።