የባዮ ሜዲካል ኢንጅነሮችና ቴክኖሎጅስቶች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የህክምና መሳሪያዎችን መጠገን ጀመሩ

  • Time to read less than 1 minute
news

በክረምት የሚሰጠው የበጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት አንድ አካል የሆነው የባዮ ሜዲካል ኢንጅነሮችና ቴክኖሎጅስቶች የህክምና መሳሪያዎች ጥገና ስራ ማስጀመሪያ ፕሮግራም የጤና ሚኒስትሮች፣የጳውሎስ ሆስፒታል ዋና ፕሮቮስትና የማኔጅመንት አባላት እንዲሁም በጎ ፈቃደኞች፣ አስመጭና አምራች ድርጅቶች በተገኙበት በጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ተካሂዷል፡፡


የጤና አገልግሎት ህይወት የሚሰጥበት የበጎ ፈቃድ አገልገሎት መሆኑን የጠቀሱት የጤና ሚንስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሰሩ ከሚገኙ ነጻ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት በተጨማሪ የባዩ ሜዲካል ኢንጅነሮችና ቴክኖሎጅስቶች ወደ በጎ ስራ አገልግሎቱ መግባታቸው ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርና በሁሉም ዘርፎች ሀገርን ዝቅ ብሎ ማገልገል ክብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡


ኢትዮጵያ ከኛ ብዙ ነገር ትጠብቃለች ያሉት ዶ/ር መቅደስ ያገለገሉ የህክምና መሳሪያዎችን ጠግኖ ወደ አገልግሎት ማብቃት ከሚቆጥበው ገንዘብ በተጨማሪ የዕውቀት ሽግግርና ለቀጣይ ጊዜያት የሚጠቅም ልምድ የሚገኝበት መሆኑን ጠቁመው እያገለገለን ያለ ጤና ተቋምን በማገዝና በማጠናከር እንዲሁም ለመደገፍ እጅን በመስጠት በጋራ አሻራ እንድናኖር ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡን በቅርበት የሚያገለግሉ የጤና ዘርፍ ባለሙያዎችንና ሰራተኞችንም አመስግነዋል፡፡


የባዮ ሜዲካል ኢንጅነሮችና ቴክኖሎጅስቶች ማህበር ፕሬዘዳንት ኢንጅነር አሸብር ወርቁ በበኩላቸው እንደ ማህበር በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት በርካታ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን መስራታቸውን አስታውሰው አሁን በክረምት በጎ ፈቃድ በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን በቀጣይም ልምዳቸውን ወደ ክልሎች በማስፋት የማገልገል ዕቅድ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡


ለ23 ቀናት የሚሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 17 አስመጭዎች 7 አምራቾችና 3 መንግስታዊ ድርጅቶች እንዲሁም 179 በጎ ፈቃደኞች የተሳተፉበት ሲሆን በአዲስ አበባ በሚገኙ 13 ሆስፒታሎች የሚገኙ 3000 ያህል የህክምና መሳሪያዎችን በመጠገን ከ47 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ለማዳን ታቅዷል፡፡


#በጎነት_ለጤናችን
#የክረምት_በጎ_አድራጎት
#የክረምት_ነጻ_የበጎ_ፍቃድ_የጤና_ምርመራና_ህክምና