ጤና ሚኒስቴር ከኮሪያው ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ የጤና እንክብካቤ ፋውንዴሽን (ኮፊ) ጋር በመተባበር የህክምና አገልግሎት መስጫ መሳርያዎች ማደሻና ማሻሻያ ማዕከል ግንባታ መጀመር የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
በግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ የቆየ ወዳጅነት ያላቸው፣ በክፉና ደግ ጊዜያትም በአብሮነታቸው የጸኑ ሀገራት ናቸው ያሉት ዶ/ር መቅደስ ይህንን ሃገራዊ የህክምና መገልገያ እቃዎች ማደሻና ማሻሻያ ማዕከል ከደቡብ ኮሪያ መንግስት ጋር ስንጀምረው በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ከመተማመናችንም በላይ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት እና ትስስር የበለጠ እያጠናከርንም ጭምር ነው ብለዋል።
በሃገራችን ታድሰው ዳግም አገልግሎት መስጠት እየቻሉ በርካታ የሕክምና መሣሪያዎች ለብክነት እየተዳረጉ እንደሚገኙ ዶ/ር መቅደስ ገልጸው ግንባታው ዘመናዊ ከመሆኑ ባሻገር የጤና አጠባበቅ መሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ለማሳደግ የምናደርገውን ጉዞ የሚያሳይ ትልቅ ምዕራፍ ነውም ብለዋል።
አምባሳደር ጁንግ ካንግ በበኩላቸው÷ ኮሪያ ሪፐብሊክና ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ የልማት መስኮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸው የባዮሜዲካል እድሳት እና ዳግም ምህንድስና ማዕከል ግንባታ ለመጀመር የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጥነው ፕሮጀክትም እንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ግንባታው በኮሪያው ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ የጤና እንክብካቤ ፋውንዴሽን (ኮፊ) በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄድ ነው።