የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የጄኤስአይ ዋና ስራ አስፈጻሚና ፕሬዝደንት ማርጋሪት ክሮቲ እና የጂኤስአይ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ተደርገው አዲስ የተሾሙት ዶ/ር ቢኒያም ደስታ ጋር ተወያዩ ።
የጄኤስአይ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር መሰየሙ በጤና ሚኒስቴር እና ጄኤስአይ መሃል ያለውን ትብብር እና ግንኙነት እንደሚያጠናክር የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በውይይታቸው የገለጹ ሲሆን፤ ጄኤስአይ የጤና ሚኒስቴር ጠንካራ አጋር መሆኑን እና ጤና ሚኒስቴር አጋርነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ጄኤስአይ ከጤና ጋር በተያያዘ እናቶች እና ህጻናት፣ የጤና ኤክስቴንሽን፣ የጤና መረጃ፣ የጤና ተቋማትን መልሶ ማቋቋም፣ አርብቶ አደር ማህበረሰቦችን መደገፍ እና ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶችን በኢትዮጵያ እየተገበረ እንደሚገኝ እና ወደፊትም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ጤና ሚኒስቴር ከጄኤስአይ ጋር በትብብር መተግበር እንደሚፈልግ ዶ/ር ደረጀ አስረድተዋል፡፡ ድርጅቱ እስካሁንም በጤናው ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ በጤና ሚኒስቴር ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጄኤስአይ በ23 ሃገራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ያስረዱት ደግሞ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርጋሪት ክሮቲ ሲሆኑ፤ አዲስ የተሰየመው የጄኤስአይ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር የድርጅቱን የተለያዩ ፕሮጀክቶች በአንድ በማስተባበር በተቀናጀ መልኩ ለመተግበረ ይረዳል ብለዋል፡፡
ጄኤስአይ ላለፉት 30 አመታት በኢትዮጵያ ከ60 በላይ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ እንደሚገኝ ያስታወሱት አዲስ የተሾሙት የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶ/ር ቢኒያም ደስታ፤ በበኩላቸዉ ጄኤስአይ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ሲተገበሩ የነበሩ የጄኤስአይ ፕሮጀክቶችን በአንድ አስተሳስሮ ለመምራት እንዲያስችል እንድሁም የክልል ጄኤስአይ ቢሮዎችም በተመሳሳይ በአንድ ቢሮ ስር ተጠቃለው ስራቸውን እደሚያከናውኑ አክለው ገልጸዋል፡፡
ዩኤስኤአይዲ ከጄኤስአይ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የጤና ስርአት ለማሻሻል እንደሚሰራ የዩኤስኤአይዲ ኢትዮጵያ የጤና ጥራት አጠባበቅ የፓርቲ ምክትል ሀላፊ የኔአለም ታደሰ በበኩላቸው የገለጹ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስት በጤና ስርአቱ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች የሚሰጠውን እንክብካቤ ለማሻሻል የደህንነት እና የጥራት ስትራቴጂ ነድፎ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ዩኤስኤአይዲ ይረዳል ብለዋል።