በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጤናው ዘርፍ የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራዎች ማስጀመርያ መርሀ ግብር ተካሄዷል። በዚህም የቤት እድሳት፣ የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ፣የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ተካሂደዋል ።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲሊ ሀሰን እንደተናገሩት በክልሉ በሚደረጉ ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቅሳሴዎች ውስጥ ጤና ዋነኛው መሆኑን ጠቁመው የክልሉን ማህበረሰብም የጤና አገልግሎት ለማሻሻል እና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰሩ ላሉት ተግባራት ጤና ሚኒስቴር እያደረገ ላለው ድጋፍ በክልሉ መንግስትና ህዝብ አመስግነዋል።
ጤናን ጨምሮ የዜጎቻችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የምናረጋግጠው በመደጋገፍ እሳቤ እና በጋራ ተቀናጅተን መስራት ስንችል ነው ብለዋል ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሀሰን።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው የጤናው ዘርፍ የክረምት በጎ አድራጎት ትግበራ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በነጻ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ፣ የችግኝ ተከላ፣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የቤት እድሳት ፣ የመማርያ ቁሳቁስ ድጋፍ፣ በበጎ ፍቃድ ደም የማሰባሰብ ስራ እና ሌሎች የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራዎችን በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስስትሯ ገለጻ በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፍቃድ ተግባር በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚገኙ ለህክምና የሚያገለግሉ ዕጽዋትን እየተተከሉ መሆናቸውንና በየጤና ተቋማት ብልሽት ገጥሟቸው አገልግሎት መስጠት ያልቻሉ የህክምና መስጫ መሳርያዎችን ብፕጥገና ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ የጤናው ዘርፍ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ለ500 ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ በመደገፍ ፣የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት፣ የችግኝ ተከላ እና የነጻ የጤና ምርመራና እድሳት በማስጀመር ፕሮግራሙ በይፋ በተግባር ተጀምሯል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው የክረምት የጤና በጎ ፍቃድ አገልግሎት ነጻ የአይን ምርመራ፣ ነጻ የስኳር በሽታ ምርመራ፣ ነጻ የደም ግፊት ምርመራን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶች በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች እንደሚሰጡ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ክቡር አቶ ወልተጂ በጋሎ ናቸው።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጤናው ዘርፍ የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራዎች ማስጀመርያ መርሀ ግብር ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የክልሉ ም/ ርዕሰ መስተዳደር ፣ የጤና ዘርፍ እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።