በሃገራችን የክረምት ወቅት መግባት ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ወረርሽኞች ስርጭት ሊጨምር ስለሚችል የክትትል እና የመከላከል ስራዎችን አጠናክሮ መስቀጠል እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ወቅታዊ የወረርሽኞች ስርጭት መካለከልን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በተሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ አሳስበዋል፡፡
በተለይም የአየር ንብረት ለዉጥ እንዲሁም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የወባ በሽታ ስርጭት ተጋላጭነትን እንደጨመረ ያስረዱት ዶ/ር መቅደስ፤ በለፉት 2 አመታት የወባ ወረርሽኝ በአፍሪካ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ 69 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ይኖራሉ ያሉት ሚኒስትሯ፤ በተለይም በክረምት ወራት የወባ ስርጭት ሊጨምር ስለሚችል የበሽታው መከላከል እና ቁጥጥር ስራዎች ላይ ማህበረሰቡና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በንቃት እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡
መዘናጋት ለበሽታው መስፋፋት ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመግለጫው የተጠቆመ ሲሆን፤ ወባ በሃገራችን የሚገኙ 10 ክልሎች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ባለፈዉ አንድ ወር በበሽታው ለተያዙ ከሰባት መቶ ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የህክምና አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡
የማህበረሰቡን የአጎበር አጠቃቀም ለማሻሻል እንዲሁም የመድሃኒት ርጭት በተመለከተ የሚዲያ አካላት ማህበረሰቡን በማስተማር የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም ወባን እና ሌሎች ወረርሽኞችን መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ መልእክት ተላልፏል፡፡
በተመሳሳይ የኮሌራ በሽታን ለመግታት የንጹህ ውሃ አቅርቦትን ማሳደግ እና የክትባት ተደራሽነትን ለመጨመር እየተሰራ ሲሆን፤ የኩፍኝ ልየታ እና ክትባትን በተመለከተም የሚተላለፉ መረጃዎችን ማህበረሰቡ ተግባራዊ እንዲያደርግ ተጠይቋል፡፡
በሃገራችን በተከሰቱ ሰው-ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰቱ ወረርሽኞች ስርጭት መጨመሩን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ያስረዱ ሲሆን፤ የተከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ከፍተኛ ርብርብር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዝግጁነት፣ የክትትል፣ መከላከል እና ምላሽ አሰጣጥ በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ ያስረዱ ሲሆን፤ ኢንስቲትዩቱ የትኛውም የጤና ስጋቶችን በመለየት የክትትል፣ የመከላከል እና ምላሽ የመስጠት ስራዎችን የሚሰራ መሆኑን በመጥቀስ፤ በተለይም ብዛት ያላቸዉ ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራ በመሰራቱ በበሽታዎቹ ይደርስ የነበረውን ጉዳት መቀነስ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
የጸጥታ ስጋት ያለባቸው አካበቢዎች በተለየ መልኩ የመድሃኒት ስርጭት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ገልጸው፤ የወባ መመርመሪያ እና መድሃኒት ስርጭት እንዲሁም የወባ ስርጭትን ለመከላከል የሚያገለግል አጎበር እና ጸረ-ወባ ትንኝ መድሃኒት እና ግብአቶች ስርጭት መካሄዱን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ የወባ መድሃኒቶች ቁጥጥር ስራ መሳራቱንም አስረድተዋል፡፡
የመግለጫውን ሙሉ ሃሳብ ከዚህ በታች በተያያዘዉ ሊንክ ማግኘት ይቻላል፡፡
https://docs.google.com/document/u/0/d/1MAwi_M0vafL8Y7IkOc946mfucCgMsCnd/edit?usp=drivesdk&rtpof=true&sd=true&fbclid=IwY2xjawEhWYNleHRuA2FlbQIxMAABHURH5geYLxNsIcnN4gFJRLKaGCP0A50u4ARfboQQgFPGZcpR5wMKuNCz0A_aem_zv4jD22MvqlyQvlUFn3PZA&pli=1