ጤና ሚኒሰቴር ከኢትዮጵያ ጤና ትምህርትና ፕሮሞሽን ባለሙያዎች ማህበር እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ሶስተኛውን ሃገር አቀፍ የማህበራዊ እና ባህሪ ለውጥ ጉባዔ “የማህበራዊ እና ባህሪ ለውጥ ተግባራት ለዘላቂ የጤና ልማት” በሚል መሪ ቃል ከ13 አለም አቀፍ አገራት ከመጡ የዘርፉ ባለሙያዎችን ጨምሮ 400 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት በአዲስ አባባ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ አገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ በሆነው ወሳኝ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በምዕተ ዓመቱ ግብ ላይ በተለያዩ የጤና ዘርፎች ከፍተኛ መሻሻሎችን አስመዝግባለች። እነዚህ ስኬቶች ሊገኙ የቻሉት አንድም የማህበራዊ እና የባህርይ ለውጥ በመተግበሩ ነው፡፡ የማህበራዊ እና የባህርይ ለውጥ ፕሮግራም፣ በሽታን ለመከላከል፣ በአጠቃላይ ለጤና ስርዓቱ ውጤታማ ለማድረግ ቁልፍ መሳሪያ ነው። እንዲሁም ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት፣ በሁሉም መርሃ ግብሮች ውስጥ አስፈላጊ ስትራቴጂ ነው። የጤና ሚኒስቴር የማህበራዊ ለውጥ ፕሮግራምን ተግባራዊ በማድረግ በጤናው ዘርፍ እምርታ ለማስመዝገብ ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በጤናው ዘርፍ እንደ ሀገር የማህበራዊ እና የባህሪ ለውጥ ለማምጣት፣ የጤና ሚኒስቴር የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ ማዘጋጀቱን የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትሯ፣ የህብረተሰባችንን የባህሪ ለውጥ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ በተለያዩ ቋንቋዎች፣ በልዩ ልዩ መድረኮች፣ በስልክ መስመሮች፣ እና በሳምንታዊ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ለማህበራዊ የባህሪ ለውጥ ስኬት፣ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የአለም አቀፍ የጆንስ ሆፕኪንስ ሴንተር ፎር ኮሙኒኬሽን ፕሮግራሞች ላይ ከፍተኛ አበርክቶ የነበራቸውን ዶክተር ቤንጃሚን ሎዛሬ ህልፈትን አስመልክቶ የህሊና ፀሎት ያስደረጉት በUSAID የማህበራዊ እና የባህርይ ለውጥ ኃላፊ ዶክተር ጉዳ አለማየሁ፣ ጤናማ ሰዎች ውጤታማ ናቸው ብለን እናምናለን፤ ጠንክረው ከሰሩ ለሀገር ዘላቂ ልማት አስተዋፅዖ ያደርጋሉ፤ ይህ ሊሳካ የሚችለው ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች እና ማህበረሰቦች የራሳቸውን ጤና እንዲያመርቱ ያልተቋረጠ የማስተማር ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች ልማድ ሆነው ሲተገበሩ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጤና ትምህርትና ፕሮሞሽን ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት፣ ዶክተር እሸቱ ግርማ በበኩላቸው የጉባዔው ዋና ዓላማ በማህበራዊ የባህሪ ለውጦች ላይ ያሉ ስራዎች፣ ልምዶችን መቀመር እርስበርስ መማማር ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር እሸቱ አክለውም ስለጤናው የሚጠይቅና የሚያውቅ ማህበረሰብ ለመፍጠር የማህበራዊ እና የባህርይ ለውጥ ተግባቦት ትልቅ ሚና አለው ብለው፣ አገራችን ኢትዮጵያ ኤች አይቪን ጨምሮ አለም አቀፍ ወረርሽኝ የነበረውን የCOVID-19 ለመከላከል የማህበራዊ እና የባህርይ ለውጥን ተጠቅመንበት ያመጣነው ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ጤና ኮሚዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ይኼ ጉባዔ በአገራችን ለሶስተኛ ጊዜ እየተካሄደ መሆኑን፣ እ.ኤ.አ. በ2016 አዲስ አበባ ላይ የመጀመሪያው አለም አቀፍ ጉባኤ ተካሂዶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ጉባኤዎቹ ትልልቅ የማህበራዊ እና የባህሪ ለውጥ ጉዳዮች የተነሱባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው አስቀድሞ በሽታ መከላከል ላይ እንደመሆኑ ህብረተሰቡ ጤናውን እንዲጠብቅና የራሱን ጤና እራሱ እንዲያመርት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ አዘውትሮ መስጠት እንደሚያስፈልግ ለዚህም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ዶክተር ተገኔ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ የ USAID ምክትል ሚሽን ዳይሬክተር ኤልኖር ታንፕን ኮ፣ የUNICEF/Ethiopia ምክትል ኃላፊ የማሪኮ ካጎሺማን ንገረግር ያደረጉ ሲሆን የመንግስታዊ ተቋማት፣ የማህበራዊ እና ባህሪ ለውጥ ባለሙያዎች፣ የሙያ ማህበራት፣ አጋር ድርጅቶች፣ የምርምር ተቋማት፣ የግሉ የጤናው ዘርፍ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት ይገኛሉ፡፡
በጉባኤዉ በጤና መህበራዊና ባህሪ ለዉጥ ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት እዉቅና ተሰጥቷል።