"በኑክሌር መስክ ዓለም አቀፍ ትብብር!" በሚል መሪ ቃል በቪየና ኦስትሪያ በተካሄደዉ 66ኛው የIAEA ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ተሳትፈዋል፡፡
በኤጀንሲው ዋና መስሪያ ቤት በቪየና ኢንተርናሽናል ሴንተር (VIC) በቪየና ኦስትሪያ የተካሄደዉ ይህ ጉባኤ ከኒዩክሌር ቴክኖሎጂ እና ሳይንስ ዙሪያ ለህክምና አገልግሎት ጥቅም የሚዉሉ ቴክኖሎጂዎችን በተለይም የካንሰር ጨረር ህክምናን ጨምሮ ለተለያዩ ህክምና ዘርፎች ጥቅም ላይ በሚዉሉ የኑክሌር ቴክኖሎጂ እና ሳይንስ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በ66ኛው የIAEA ጠቅላላ ጉባኤ የኢትዮጵያ ተወካዮች ከአክሽን ፎር ካንሰር ቴራፒ (PACT) መርሃ ግብሮች ቡድን ጋር በቀጥታ ውይይት በማድረግ በኢትዮጵያ እና በIAEA መካከል ስላለው እና የወደፊት የቴክኒክ ትብብር በተመለከተም ተወያይተዋል።
ከአክሽን ፎር ካንሰር ቴራፒ (PACT) በኢትዮጵያ የካንሰር ጨረር ህክምና ላይ በትብብር የሚሰራዉን ሰራ በማጠናከር የተቀናጀ ያአገሪቱ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የጋራ ዕቅድ ለማውጣት መግባባት ላይ ተደርሷል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከ IAEA ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማሪያኖ ግሮሲ ጋር በጽህፈት ቤታቸው በመገኘት የጋራ ዉይይት አድርገዋል፡፡
በዉይይቱም IAEA በኢትዮጵያ የካንሰር መከላከልና ህክምና ጋር ባለው ትብብር ዙሪያ እና በቀጣይ የትብብር አቅጣጫ ላይ በስፋት ዉይይት ተደርጓል፡፡
ክቡር ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የካንሰር ህክምናን በማስፋፋት ረገድ ኢትዮጵያ እና IAEA ያደረጉትን የረጅም ጊዜ አጋርነት እና ትብብርን በማድነቅ ይሄዉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። በጉባኤዉም ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የIAEA አባል ሀገራት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡