መድሃኒት የተላመደ የቲቢ በሽታ ከተስፋፋባቸው 33 ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ መውጣቷ መልካም አጋጣሚ ነዉ።

  • Time to read less than 1 minute
Dr. Lia Tadesse

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መድሃኒት የተላመደ የቲቢ በሽታን መግታት የድርጊት መርሃ ግብር ተቀብላ እየሰራች ነዉ ያሉት የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ናቸው፡፡ ክብርት ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት በምስራቅ መካከለኛና ደቡብ አፍሪቃ (ECSA) ዓመታዊ የቲቢ በሽታ ምርመራ ላብራቶር የማጠናከሪያ ውይይት መድረክ ላይ ነዉ። በአገራችን በቲቢ መከላከል ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች አበረታች ለውጥ እያሳዩ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ በዋቢነትም በዓለም መድሃኒት የተላመደ የቲቢ በሽታ ከተስፋፋባቸው 33 ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ መውጣቷ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።


የECSA ዳይሬክተር ጀኔራል ፕ/ር ዮስዋ ደምብስያ እንደተናገሩት የአፍሪካ ችግሮች ለአፍሪካኖች እንዲፈቱ አስታውሰው በግሎባል ፈንድ የቲቢ ላብራቶር ምርመራ ማጠናከሪያ ኘሮጀክት ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲያግዙ ለቆዩ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበው ለወደፊትም ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፋቸው እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡


ቲቢን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው ላይ እንደ ተግዳሮት ከተገለጹት አበይት ምክንያቶች ማካከል የመመርመሪያ ቁሳቁስ የሞለኪዩላር ምርመራ(geneXpert)  ቁጥር ከአገሪቷ ፍላጎት አንፃር አለመመጣጠን፣ የምርመራ ጊዜ መዘግየት፣ የምርመራ አቅም ማነስና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው፡፡ 


መድረኩም ከ19 ሀገራት የተውጣጡ የላብራቶሪ ባለሙያዎች፣ አጥኝዎች፣ የአገራት ተወካዮች፣ ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ዩ.ኤስ.ኤአይ.ድ፣ ሲ.ዲ.ሲ እና የተለያዩ አጋር አካላት የተገኙበት ሲሆን ለሁለት ቀን የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል፡፡