በጉባዔው ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አየለ ተሾመ የማህበሩ አባላት በግለሰብም ደረጃም ሆነ እንደ ተቋም ሃገር በተቸገረችበት ጊዜ ሁሉ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች በተለይም በጦርነት ጉዳት ለሚደርስባቸው የኢትዮጵያ ጀግና ሰራዊት አባላትን ህይወት ለመታደግ ላበረከቱት እና እያበረከቱት ያለው አገልግሎት በታሪክ መዝገብ ላይ መፃፉን ጠቅሰው ለአበርክቶዓቸው ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግናለች ብለዋል።
ዶ/ር አየለ አክለውም እንደ ሃገር በማህበርሩና የህክምና ኮሌጆች ጥረት ከተለያዩ ረጂ አካላት ጋር በሚደረጉ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ለአጥንት ህክምና የሚያስፈልጉ የህክምና መሳሪያዎችና ግብአቶችን እንዲቀርቡ በማድረግ የአጥንት ህክምና ፍላጎትን ለማሟላትና ተደራሽ ለማድረግ የሚያከናውኗቸው ተግባሮች የጤና ሚኒስቴር ሁሌም በታላቅ አድናቆት የሚያነሳው እንደሆነ አንስተዉ ለነሱም ሆነ የህክምና መሳሪያና ግብአት ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ድርጅቶችም በተገልጋዩ ማህበረሰብ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
ሚኒስቴር ዴኤታው በማከልም አሁን ያለንበት ወቅት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሚበዙበት፣ የማህበረሰባችን ፍላጎትና ባለቤትነት የጨመረበት በመሆኑ የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል በመሰረተ ልማት፣ በሰው ሃብት ልማት እና በግብዓት አቅርቦት ዙሪያ ከምንሰራቸው ስራዎች በተጨማሪ የጤና አገልግሎት ስርአቶቻችንን በመከለስና በማሻሻል ባለን ውስን የሰው ሃብትም ሆነ ሌሎች ግብዓቶች ውጤታማነትን በማሻሻል፣ ብክነትን በመቀነስ እና የአገልግሎት ጥራትና የተገልጋይ ደህንነትን የሚያረጋግጡ አዳዲስ አሰራሮችን ወደ ተግባር የምናስገባበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በዚህም የስፔሻሊቲና ሰብስፔሻሊቲ አገልግሎትን ለማሻሻል የሚረዳ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ትግበራ፣ በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ የሚስተዋሉ የስርአት ማነቆዎችን ለማሻሻል የሚረዳ የሪፎርም ፓኬጅም እየተተገበረ ፥ ሲሆን ያልተቆራረጠ የግብአት አቅርቦትን ለማረጋገጥ የሚረዱ የመንግስትና የግሉ ሴክተር በጋራ የሚሰሩባቸው የተለያዩ የትብብር ማዕቀፎችን ወደ ስራ ለማስገባትም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የሙያ ማህበሩና ባለሙያዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለውጤታማነቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በእለቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ እና በዚህ አመት ጉባኤውን ትኩረት ሰጥቶ የሚነጋገርባቸውን ርዕሶች ያስተዋወቁት የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ገለታው ተሰማም ባለፉት ኣመታት በነበሩ ጦርነቶች ምክንያት የማህበሩ አባላት ለነበራቸው የነቃ ተሳትፎ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም በግጭት ወቅትና በተለይም በድህረ-ጦርነት ተጎጂዎች ሊያገኙ ስለሚገባቸው አገልግሎቶችና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ የሚሰጠውን ዘመናዊ ህክምና ምን መምሰል እንደሚገባው ሰፊ ውይይት እንደሚደረግና ልምድ ያላቸው ሀገራት ተሞክሮም በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባካበቱና በጉባኤው በእንግድነት በተገኙ ባለሙያዎች የሚቀርብ እንደሚሆን አውስተዋል።
በጉባኤውም በማህበሩ ውስጥ በአጥንት ህክምናው ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱና ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ለነበሩ የህክምና ባለሙያዎችና ተቋማት የምስጋናና የዕውቅና ሽልማት የመስጠት ስነ ስርዓት የተከናወነ ሲሆን ለአጥንት ህክምና የሚውሉ የህክምና መሳሪያዎችንና ሌሎች ግብአቶችን የሚያቀርቡ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለእይታ ያቀረቡበት ኤግዚቢሽንም በይፋ ተከፍቶ በእንግዶችና ተሳታፊዎች ተጎብኝቷል።