የዘንድሮው አመታዊ አገራዊ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር እቅድ የክልል እና ከተማ መስተዳድር ጤና ቢሮዎችን እና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ጽህፈት ቤቶችን ሴክተር መስሪያ ቤቶችን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ የ2014 በጀት አመት አፈጻጸምን በመገምገም 2015 በጀት አመት እቅድ ዝግጅት የጋራ ለማድረግና ቀጣይ እርምጃዎችን ለማፋጠን ይረዳ ዘንድ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይወት ሰለሞን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ አካላት ሲመራ የነበረው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ስራ አዲስ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በአንድ እንዲመራ መደረጉ መልካም ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን አቅጣጫ በማሳካት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን በ2030 ለማስቆም መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ይህንንም ለማሳካት ባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉና እስካሁንም ላደረጉት አስተዋጽኦና ተሳትፎ ዳይሬክተሯ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጤና ሚኒስቴር ለስራ አመቺ ሁኔዎችን በመፍጠርና አጋር በመሆን ስላደረገላቸው ትብብር ምስጋና ያቀረቡት የፔፕፋር ካንትሪ ሪፕረሰንታቲቭ ዶ/ር ኤይሚ ሩራንግዋ፤ ድርጅታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራ እና ምክር አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የማህበረሰብ ተሳትፎ ቫይረሱን ለመግታት ወሳኝ መሆኑን ዶ/ር ኤይሚ አክለው ገልጸዋል፡፡
ባለፉት 20 አመታት በተደረገ ቅንጅት በሽታውን ለመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎች አመርቂ መሆናቸውን የገለጹት የኔፕ ፕላስ ስራ አስኪያጅ ዳይሬክተር አቶ ባይሳ ጫላ ሲሆኑ፤ አሁንም መድሎ እና ማግለልን ለመቀነስ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አቶ ባይሳ በመድረኩ ላይ እንዳሉት "በጋራ ያቀድነውን እቅድ በጋራ ተግባር ላይ ለማዋል መስራት አለብን"፡፡
በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፈቃዱ ያደታ በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ብሔራዊ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ፕሮግራም አቅጣጫ የቀረበ ሲሆን ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ጥራት እና ፍትሃዊ ተደራሽነት ማሻሻል እንዲሁም የማህበረሰቡን ተሳትፎና ባለቤትነት ማሻሻል የ2015 ስትራቴጂክ አቅጣጫዎች ዋነኛ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ የ2015 በጀት አመት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ፕሮግራም መነሻ ኢላማዎች እና ዋና ዋና ተግባራት እቅድም በመድረኩ ላይ ቀርቧል፡፡
የክልል እና ከተማ መስተዳድር ጤና ቢሮዎች እና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ጽህፈት ቤቶች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቀረበው እቅድ ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡