“ምቹ ሁኔታ ለሚያጠቡ እናቶች፤ እናስተምር፤ እንደግፍ!!” በሚል መሪ ቃል የዘንድሮው የጡት ማጥባት ሣምንት በዓለም ለሰላሳኛ በሀገራችን ደግሞ ለአስራ አራተኛ ጊዜ እየተከበረ ነው፡፡
የሥርዓተ ምግብ ችግሮች በዓለም ላይ በየዓመቱ ወደ አምስት ሚሊዮን ሕፃናት ህመምና ሞት ምክንያት ነው ያሉት የጤና ሚኒስቴር የእናቶች ህፃናት እና የስርዓት ምግብ ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም ከፅንስ ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜ ባለው ጊዜ ማስተካከል ካልተቻለ መቀንጨር እና ሌሎች የምግብ አለመመጣጠን ችግሮች ሊከሰት እና በቀጣዩ የእድሜ ክልል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል አመጋገብ ችግር ይሆናል ብለዋል።
እናቶች እንደወለዱ በመጀመሪያ የሚገኘውን እንገር የተሰኘ የጡት ወተት ለልጁ በመስጠት የልጁን ጤንነት በመጠበቅ በኩል ልክ እንደክትባት አስፈላጊ በመሆኑን፤ ማንኛዋም እናት ልጅዋን ከወለደችበት ባለው የአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ጡት ማጥባት ማስጀመር እና እስከስድስት ወር ድረስ ካለምንም ድብልቅ የጡት ወተቷን ብቻ መስጠት እንዲሁም ሁለት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ከተጨማሪ ምግቦች ጋር ጡት ማጥባትን መቀጠል የእናቶች ታላቅ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
እናቶች ጡት ማጥባትን በማይመች ሁኔታም ውስጥም ሆነው በመደገፍ የዘላቂ ልማት ግባችንና በሃገራችን የተቀመጠውን የምግብ አለመመጣጠን ችግርን በመቅረፍ የሕፃናት ሞትንና ሕመምን ለመቀነስ ይቻል ዘንድ የሁሉም ተቋማትና ሕብረተሰብ ክፍሎች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ዶ/ር ጄን ሞይታ የዮኒሴፍ ተወካይ ባቀረቡት ንግግር የእናት ጡት ወተት የህይወት ሥጦታ፤ የህይወት ምግብ በተፈጥሮ የተሰጠ እንደመሆኑ እናቶች ከወለዱበት ሰዓት ጀምሮ ማጥባት እንዳለባቸው ገልፀው ለዚህም የሁሉም አካላት ድጋፍ የመስጠት ሀላፊነት ነው ብለዋል።
በኮቪድ ወረርሽኝ፣ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ወቅት ለጡት ማጥባት ምጩ አካባቢና ሁኔታዎችን በመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት፤ መንግስት፣ የግል ተቋማትና አጋር ድርጅቶች እንዲሁም ማህበረሰቡ ጡት ማጥባትን ለመጠበቅ፣ ለማስተዋወቅ እና ለመደገፍ ጥረት እንዲኖር በዝግጅቱ መልዕክት ተላልፏል፡፡
በዝግጅቱ የፌደራል የምግብና ሥርዓተ ምግብ ተጋባሪ ሴክተር ሀላፊዎችና ተወካዮች፣ የአጋር ድርጅቶች ሀላፊዎችና ተወካዮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።