በዛሬው እለት የተደረገው ድጋፍ 9 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የላብራቶሪ እቃዎች መሆናቸው ማወቅ የተቻለ ሲሆኑ ድጋፉ የተደረገው በአማራ እና በአፋር በክልል ለሚገኙ ስድስት ሆስፒታሎች ሲሆን በስድስቱ ሆስፒታሎች ውስጥ ላሉ የላብራቶሪ ክፍሎችን መልሶ ለማደረጃት የሚረዳ ድጋፍ ነው፡፡
በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት በአገራቱ የነበረው ጦርነት የጤና ተቋማትን ማውደሙን ተከትሎ መልሶ ለማቋቋም በተደረገው ርብርብ ሁሉም ሆስፒታሎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን አንስተዋል፡፡ ኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ግሎባል ዋን ሄልዝ ፕሮግራም ለዚህ ችግር ትኩረት በመስጠት የሆስፒታሎችን ላብራቶሪዎች ሙሉ ለሙሉ ለመደገፍ መቻሉን ዶክተር ሊያ የተናገሩ ሲሆን በቴክኒክም የማጠናከር ስራ እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ድጋፉ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ድጋፍ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የላብራቶሪ እቃዎች ድጋፍ መድረጉንም አስታሰው በዛሬው እለትም የዘጠኝ ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ድጋፉም በጤናው አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራት ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት እና አጠቃለይ የጤናውን ስርኣት ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል፡፡
ዶክተር ሊያ ድጋፉን ላደረገው ለኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ግሎባል ዋን ሄልዝ ፕሮግራም እና ድጋፉን እንዲደረግ ፋይናንስ ላደረገው ለዩ ኤስ ሲዲሲ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ግሎባል ዋን ሄልዝ ፕሮግራም ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንዳሉት በአገሪቱ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ከተጎዱ ተቋማት መካከል የጤና ተቋማት እንደሚገኙበት ጠቅሰው የኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ችግሩ ላይ ተወያይቶ ድጋፉን ለማድረግ እንደቻለ አስታውቋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንጻር ቀደም ሲል በመጀመሪያ ዙር ከተደረገው 5.6 ሚሊዮን ብር ድገፍ በተጨማሪ ዛሬም 9 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ድጋፍ ማድረግ መቻሉንና በአጠቃላይ ዘጠኝ ሆስፒታሎችን ለመደገፍ መቻሉን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
የኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ግሎባል ዋን ሄልዝ ፕሮግራም የጤናው ስርዓትን የማጠናከር፣ የአቅም ግንባታ፣ የላብራቶሪ ግንባታ እና ማስፋፊያ ስራዎችም እንደሚሰራ ገልጸው አዳዲስ ላብራቶሪ በአዳማ፣ በባህርዳር፣ በአርባምንጭ እና አዲስ አበባ ግንባታዎች እንደሚሰሩ በንግግራቸው አንስተዋል፡፡ በቀጣይም ተቋሙ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር በመሆን ለመስራት እና የጤናውን ዘርፍ ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
በዩኤስ ኢምባሲ የሲዲሲ ኢትዮጲያ ተወካይ ሚስተር ማቲው ሲ.ኦሰቲን በበኩላቸው ድጋፎቹ የተደረጉት የነበረው ግጭት ባደረሰው ተጽእኖ ምክንያት በቦታው የሚኖረው ህብረተሰብ ጥራት ያለው መሰረታዊ የጤና እንክብካቤና አገልግሎት የማግኘት ችግር እንዳጋጠመው በመረዳት መሆኑን ገልጸው ሲዲሲ ጥራቱን የጠበቀ የላራቶሪ አገልግሎት ላይ ያለውን ክፍተት ለይቶ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ተጎጂ በሆኑ የአማራ እና አፋር ክልሎች የጤና አገልግሎትና ግብአት አቅርቦት ለማሻሻል እና መልሶ የማቋቋም ስራውን በቀጣነት ለመደገፍ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ እና ከሌሎች አጋሮች ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ዶክተር ሊያ የኬሚስትሪ ማሽንና ሌሎች የተደረጉት ድጋፎች ከዶክተር ኤባ አባተ እና ከሚስተር ማተው ሲ.ኦሰቲን እጅ ተረክበዋል፡፡