የ100 የልብ ህሙማን ህጻናት ህክምናና የአየር ቲኬት ሙሉ ወጪ በመሸፈን ህንድ ሃገር ለማሳከም የመግባቢያ ሰነድ በጤና ሚኒስቴር፣ በኢትጵያ አየር መንገድ፣ በሮታሪ ኢንተርናሽናል እና በኢትጵያ ልብ ህሙማን ማህበር የተፈረመ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሚሰራውን ስራ የሚያጠናክር የመግባቢያ ሰነድ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡
በመንግስት ተቋማትና በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማእከል ብቻ ከ7,000 በላይ ህጻናት ለልብ ቀዶ ህክምና ወረፋ እየጠበቁ እንደሚገኙ የተናገሩት ዶ/ር ሊያ፤ እነዚህን ችግሮች ታሳቢ ባደረገ መልኩ ዛሬ ሁለት የመግባቢያ ሰነዱች እንደተፈረሙ ገልጸዋል፡፡
የመጀመሪያው የመግባቢያ ሰነድ የ100 ታካሚ ህጻናቱን ሙሉ ወጪ ከነአስታማሚዎቻቸው በሮታሪ ኢንተርናሽናልና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሸፈን የሚያስችል ሲሆን፤ የልብ ማእከል ህሙማን ህጻናቱን የመለየት እና ህክምናቸውን ጨርሰው ሲመጡ በሃገር ውስጥ ክትትል ለማድረግ የሚያስችል ሲሆን፤ ጤና ሚኒስቴር ከታክስ ጋር የተያያዙ ከፍያዎችና ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለማከናወን የሚስችል ስምምነት ነው፡፡
ሁለተኛው የመግባቢያ ሰነድ ደግሞ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ መካከል በማዕከሉ የሚሰጠዉን እገለገሎት በዘላቂነት ለማጠናከር ተፈርሟል፡፡
የኢትዮጵያ አየርመንገድ 100 የአየር ትኪት ለታካሚ ህጻናቱ እና 100 ቲኬት ለህጻናቱ ወላጆች በነጻ ለማቅረብ ስምምነት በመደረጉ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት የአየርመንገዱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ጣሰው ናቸው፡፡ ይህ የመግባቢያ ስምምነት የኢትዮጵያ አየርመንገድ የማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ባቋቋመው በኢቲ ፋንዴሽን በኩል የተደረገ ሲሆን ወደ ፊትም ለኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ማህበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
የህጻናት እና እናቶች ጤና ሮታሪ ኢትዮጵያ ከሚሰራቸው የበጎ አድራጎት ስራዎች ዋነኛው መሆኑን የገለጹት የሮታሪ ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር አቶ ቶሾመ ከበደ ናቸው፡፡ ሮታሪ ኢትዮጵያ በዚህ አመት ብቻ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ፕሮጀክቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ በመስራት ለይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ለልብ ህሙማን ህጻናት ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ለወደፊትም ከአጋሮች ጋር በመተባበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ አንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን መርጃ ቦርድ በአመት ከ400 እስከ 500 ለሚሆኑ የልብ ህሙማን ህጻናት የህክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ መሆኑን ያስተወሱት የቦርዱ ሊቃ መንበር አቶ ሰለሃዲን ከሊፋ ሲሆኑ፤ ወደፊትም አገልግሎቱን በማጠናከር በአመት እስከ 1,500 ለሚሆኑ የልብ ህሙማን ህጻናት የህክምና አገልግሎት ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ የስምምነት ሰነዱን ለፈረሙ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በጤና ሚኒስቴርና በታማሚ ልጆቹ ቤተሰቦች ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡