የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በስዊዘርላንድ ጀኔቫ "ሰላም ለጤና ጤና ለሰላም!” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ባለው 75ኛው አመታዊ የአለም ጤና ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት ጤንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብን መፍጠር መቻል አስተማማኝና ዘለቄታዊ ያለው ሰላም እንዲኖር ከማድረግ አንጻር ያላው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ያለሰላም የተሟላ ጤናም መኖር አይችልም ያሉት ሚኒስትሯ በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት በርካታ የጤና ተቋማት እንደወደሙና እንደተዘረፉ በዚህም በርካታ ቁጥር ያለው ህብረተሰብ የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዳያገኝ መስተጓጓሉን ጠቅሰው የኢትዮጵያ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የጤና አገልግሎትን ወደነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁንም የመንግስትን ጥሪ በመቀበል የጤና አገልግሎቱን ወደነበረበት ለመመለስና ህብረተሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ድጋፍ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ሚኒስትሯ ከችግሩ ስፋት አንጻር አሁንም ቢሆን የአለም ማህበረሰብና የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።