የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጋራ ሊሰሩ ይገባል

  • Time to read less than 1 minute
EGAD

16ኛው አመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባኤ ላይ ከተገኙ የአጎራባች ሃገራት ተወካዮችጋር የቲቢ በሽታን መከላከልና መቆጣጠር በተመለከተ የጎንዮሽ ውይይት ተካሂዷል።

አጎራባች ሀገራት በሚዋሰኑባቸው አከባቢዎች ተመሳሳይ ማህበረሰብ የሚገኝባቸው በመሆናቸው እና በተለይም አርብቶ አደር በሚበዛባቸው የምስራቅ አፍሪካ አጎራባች አከባቢዎች የቲቢ በሽታ ህክምናን ለመስጠትም ሆነ ክትትል ለማድረግ አዳጋች በመሆኑ ሃገራቱ በጋራ መስራታቸው ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል።

በአጎራባች አከባቢዎች ያለው ነባራዊ ሁኔታን የሚያመለክት በቂ መረጃ አለመኖር እና የግብአት ውስንነት ማነቆ መሆኑን ተወካዮች አውስተው የምርምር ተግባራትን በስፋት መስራት፣ ትብብርን ማጠናከርና ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ከፍተኛ ሃላፊዎችን ማስገንዘብና የሚድያና ተግባቦት ፕላትፎርም ተፈጥሮ በትኩረት በጋራ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህ ልዩ የጎንዮሽ ውይይት በትራክ ሴክሬታሪያት የሚመራ ከየሃገራቱ የተውጣጣ የስራ ቡድን ተቋቁሞ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ማእቀፍ እንደሚዘጋጅ ታውቋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሌላንድ እና ደቡብ ሱዳን ተወካዮች እንደሁም የአፍሪካ ሲዲሲ፣ ዩኒሴፍ፣ የአለም ጤና ድርጅት፣ ጤና ሚኒስቴር፣ አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዮት እና ትራክ ሴክሬታሪያት ተወካዮች በስብሰባው የተገኙ ሲሆን የየሃገራቱ ተወካዮች የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

በተመሳሳይ ከጎንዮሽ ውይይቶች በተጨማሪ በ16ኛው የቲቢ ምርምር ጉባኤ ላይ ከ43 በላይ የምርምር ስራዎች የቀረቡ ሲሆን አብዛኛው የቲቢ በሽታና ተዛማች ችግሮች ላይ የሚያጠነጥኑ በመሆናቸው የቲቢ በሽታን በመካለከልና በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል አቶ ታዬ ለታ፣ በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር።

የቲቢ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ እየተሰሩ ያሉ የምርምር ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ ሲሆን ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በቲቢ በሽታ ላይ የተለያዩ የምርምር ስራዎች ሲሰሩ በመቆየታቸው የቲቢ በሽታ ስርጭትን በመከላከል ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ሲሉ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ታዬ ለታ ገለጻ በዚህ አመት የቀረቡ የምርምር ስራዎች የቲቢ በሽታን በዘላቂነት መፍታት በሚያስችል የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያጠነጠነ ነው።