የ2ኛ ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ ሁለተኛ ዙር የኮቪድ 19 ክትባት ዘመቻ በአገር አቀፍ ደረጃ ከየካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን በአሁኑ ዘመቻ የተሰጠውን ከ14 ሚሊዮን በላይ ክትባትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መከተብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ከሆነ 17 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ክትባት የወሰዱ ሲሆን ከአንድ መቶ ዘጠና ሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑት የማጠናከርያ ክትባቱን (Booster dose) ተከትበዋል፡፡ በጥቅሉ ከ25 ሚሊዮን በላይ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውልም ተደርጓል፡፡
በዘመቻውም በመጀመርያው ዙር የመከላከያ ክትባቱ ያልተሰጠባቸው የአማራ እና የአፋር ክልሎችን በማካተት ክትባቱን መስጠት መቻሉንም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር የተወሰዱት የመከላከል እርምጃዎች ዉጤታማ ቢሆኑም ወረርሽኙን ግን አሁንም ሙሉ በሙሉ ለማስቆም ስላልተቻለ ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ጥንቃቄ እያደረገ ጎን ለጎን ክትባቱን እንዲወስድ ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጤና ተቋማትና ጊዚያዊ የክትባት ጣቢያዎች የኮቪድ-19 ክትባት ሳይሰላቹ እንዲከተቡ ያሳሰቡ ሲሆን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እንዲሁም ባለድርሻ አካላት፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት፣ የሐይማኖት ተቋማት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል ስራው ብሎም የክትባት መርሃ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን ርብርብ እንዲያደረጉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
እስከ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ባለው መረጃ መሰረት 468 ሺ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆኑ፣ በሽታው የ7,473 ወገኖቻችን ህይወት መንጠቁን ለማወቅ ተችላል፡፡