በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት በሀገራችን ለሶስተኛ ጊዜ እየተዘከረ ባለው የአለም ትኩረት የሚሹ የሀሩራማ በሽታዎች ቀንን አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ባስተላለፉት መልእክት እንደ ዝሆኔ/ፖዶኮኒዮሲስ፣ ሊንፋቲክ ፊላሪያሲስ፣ ሀይድሮ ሲል፣ ሌሽሚያሲስ የመሳሰሉ የቆላማ እና ሀሩራማ በሽታዎች ለረጅም ዘመን ትኩረት ሳያገኙ በመቆየታቸው ዜጎችን ለተለያዩ አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች እየዳረጉ መሆናቸውን ተናግረው ይህንን ለመቀየር ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን በሁሉም ስፍራ ማዳረስ ረገድ ሁሉም በጤና ዘርፍ እየሰሩ ያሉ አካላት ተገቢ ትኩረት እንዲሰጡ፣ እንዲሁም በጋራ በመቀናጀት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አመታት ለሀሩራማ በሽታዎች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እና ስትራቴጂ በማዘጋጀት ስትሰራ እንደነበር አስታውሰው ትርጉም ያለው ለውጥም ማምጣት መቻሉን አስረድተዋል።
የሀሩራማ በሽታዎች ዋነኛ ሰበብ የግል እና የአካባቢ ንጽህና መጓደል በመሆኑ ህብረተሰቡ ንጽህናን መጠበቅ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፣ የሚመለከታቸው አካላትም ጥራት ያላቸውን አገልግሎቶች በማቅረብና አስፈላጊ ግብአት በመመደብ የሀሩራማ በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። እስካሁን ባለው ሂደትም ከፍተኛ እገዛ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የአለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር ቡሬማ ሳምቦ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሀሩራማ በሽታዎች የሰጠችውን ትኩረት አድንቀው የአለም ጤና ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
የሲዳማ ብሄራዊ ክልልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች ቀን በክልሉ መከበሩ ጤና ቢሮው ችግሩን ለማስወገድ እየሰራ ላለው ተግባር ትልቅ መነቃቃት እንደሚፈጥር በመግለጽ ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣቹ መልእክት አስተላልፈዋል።
በበአሉ ሶስተኛው ትኩረት የሚሹ የሀራማ በሽታዎችን መከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን አሁንም ለሀሩራማ በሽታዎች በሁሉም አካላት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።