የመሀል ሜዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መደበኛ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።" የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወርቅነህ ዘዉዴ 

  • Time to read less than 1 minute
Mehal Meda

በአሸባሪውና ዘራፊው ቡድን የሕክምና አገልግሎት ያቋረጠው የመሀል ሜዳ ሆስፒታል በዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታልና በአካባቢው ማህበረሰብ በተደረገለት ድጋፍ የህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወርቅነህ ዘዉዴ ተናገሩ።


ሆስፒታሉ በተደረገለት የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመድኃኒት አቅርቦት ድጋፍ የእናቶችና የህፃናት ጤና አገልግሎት፣ የድንተኛና ጽኑ ሕሙማን አገልግሎት የተመላላሽ ህክምና አገልግሎት በየእለቱ በአማካይ ከ 150 እስከ 200 ታካሚዎች አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው ሙሉ ለሙሉ ሆስፒታሉን ወደ ስራ ለመመለስ ተጨማሪ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።


በሆስፒተሉ ሲገለገሉ ያገኘናቸው ወ/ሮ አስካለ ገዛኸኝ እና አቶ በልዩ ካሳዬ ተመላላሽ ህክምና ክትትላቸው በመቋረጡ ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸው ሆስፒታሉ አገልግሎት ጀምሮ በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።


እንደ ወ/ሮ አስካለ ገለጻ ለቅድመ ወሊድ ክትትል በሆስፒታሉ እንድትገኝ ቀጠሮ ተሰጥቷት እንደነበርና የሆስፒታሉ አገልግሎት በነበረው ጦርነት በመቋረጡ ምክንያት ተጨንቃ እንደነበረ የተናገራቸው ያ የመከራ ጊዜ አልፎ ዛሬ በሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ድጋፍና ክብካቤ በሰለም መገላገሏን ተናግራለች።


አቶ በልዩ በበኩላቸው ተገቢውን የህክምና አገልግሎት በማግኘቴ የጤና ባለሙያዎችንና መንግስትን እንዲሁም ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመሰግናለሁ ብለዋል።


የመሀል ሜዳ ሆስፒታል ባለሙያ ዶ/ር ዘውዱ አረጋ እንዳሉት ከወረራው በኋላ ሆስፒታሉ በተደረገለት ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረው የአምቡላንስ አገልግሎት በመስተጓጓሉ በእናቶችና በድንገተኛ ጤና አገልግሎት ላይ ተጽእኖ አሳድሯል ብለዋል።