ጤና ሚኒስቴር ለአማራ ክልል ለወደሙ የጤና ተቋማት  አጋር አካላትን በማስተባበር ከ21 ሚሊየን ብር በላይ  የሚያወጡ የህክክምና ግብአቶችን፣ መድሀኒቶችን፣ አንቡላንሶችን እና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አስረከበ። 

  • Time to read less than 1 minute
donation

የጤናማ እናትነት ወር በደሴ ከተማ በተከበረበት ስነስርአት ጤና ሚኒስቴር አጋር አካላትን በማስተባበር ለእናቶች እና ህጻናት ጤና ከፍተኛ እገዛ ማድረግ የሚችሉ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የህክምና ግብአቶችን፣ መድሀኒቶችን፣ ሁለት አንቡላንሶችን እና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አበርክቷል። 


የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ወራሪው ሀይል ተቋሞቻችንን ቢያወድምም ጠንካራ መንፈሳችንን እና ህብረታችንን ከቶ ሊሰብር አይቻለውምና ከቀድሞ በበለጠ እጅ ለእጅ ያተያይዘን ተቋሞቻችንን እንገነባለን ሲሉ ተናግረዋል።


የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው  በአፋርም ሆነ በአማራ ክልሎች የእናቶች እና ህጻናት ጤና አገልግሎት በጦርነቱ ምክንያት ፈተና ገጥሞት መቆየቱን ገልጸው አብረው የሚሰሩ አጋር አካላትን በማስተባበር በአማራ ክልል 21 ሚሊየን የሚሆን ድጋፍ መለገስ መቻሉን ገልጸው ለአፋር ክልልም ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል። 


ድጋፉን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ  አቶ አብዱከሪም  መንግስቱ  የተረከቡ ሲሆን÷ ለተደረገው ድጋፍ አጋር አካላትንና የጤና ሚኒስቴርን አመስግነው በቀጣይ የወደሙ ጤና ተቋማት ወደ ተሟላ አገልግሎት ለመመለስ የሁሉንም ርብርብ ጠይቀዋል። 


የደሴ ሆስፒታል እና የቤተሰብ መምሪያ በደሴ ያስገነባው የስልጠና ማእከል እና ክሊኒክ ህንጻ የተጎበኙ ሲሆን በደሴ ሆስፒታል ለወለዱ እናቶችን የጤናማ እናትነት ወርን ምክንያት በማድረግ ስጦታ አበርክተዋል።