ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን አገልግሎት ተደራሽ ላልሆኑ የአርብቶ አደር የህብረተሰብ ክፍሎች

  • Time to read less than 1 minute
jigjiga

ከጥቅምት 19_21/2014 ዓ.ም በሶማል ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚካሄደው የጤናው ዘርፍ ልማት የምክክር ጉባኤ በመጀመሪያ ቀን ውሎ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ተሞክሮዎችን ምልከታ በማድረግ ጀምሯል።


በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እና በሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ  ምክትል ሃላፊ ወ/ሮ ሀዋ ሱሌማን የተመራው ቡድን ከጅግጅጋ ከተማ 55 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ጎልጃኖ ወረዳ መልካዳ ካስ ቀበሌ የመስክ ጉብኝት አካሂዷል።


በጉብኝቱም ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው የተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን አገልግሎት የስራ ተሞክሮ ታይቷል። በሶማሌ ክልል በ29 ቡድኖች የተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን እያንዳንዱ ቡድን ለስድስት ቀበሌዎች አገልግሎት ይሰጣል።


ተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን አገልግሎቱ በጤና አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑ የአርብቶ አደር የህብረተሰብ ክፍሎችን ትኩረት ያደረገ ሲሆን የምርመራ፣ የምክር አገልግሎት፣ የክትባት፣ የስነ_ምግብ፣ የእናቶችና ህፃናት፣ ከ5 አመት በታች እና የአዋቂዎች አገልግሎት በቡድኑ አባላት ይሰጣሉ።


በተንቀሳቃሽ ጤና ቡድኑ አገልግሎት እያገኙ ያገኘናቸው የመልካዳ ካስ ቀበሌ ነዋሪ ወ/ሮ ሮዴ ሁሴን የ2 አመት ልጃቸው አይኑንና ጉንፋን ታሞ ወደ አገልግሎቱ  መምጣታቸውን ተናግረው በቡድኑ ባለሙያዎች መድሀኒት ታዞላቸውና የህፃኑን አመጋገብና ንፅህና የተመለከተም የምክር አገልግሎት እንደተሰጣት ተናግረዋል።


ወ/ሮ ሮዳ መኖሪያ አካባቢያችን ድረስ ባለሙያዎች በየሳምንቱ እየመጡ እንደዚህ አይነት አገልግሎት ማግኘታችን በትራንስፓርትና በአቅም ችግር ምክንያት ወደ ጤና ተቋም ለመሄድ የተቸገረውን ወገናችንን ህይወት በቀላሉ ስለሚታደግ አመስግነው ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።


የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ከመስክ ጉብኝቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት በጤና ስርዓቱ ተደራሽ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም መድረስ እንደሚገባ የዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብ እንደሚሰጥ ገልፀው የተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን አገልግሎቱ ደግሞ የእዚህ አንድ አካል ነው ብለዋል።


ዶ/ር ደረጀ አያይዘውም በተንቀሳቃሽ የጤና ቡድኑ በርካታ የአርብቶ አደር ነዋሪዎች አገልግሎት እያገኙ መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ አገልግሎቱ  እንዲያድግ በጥናት ላይ ታግዞ ቀልጣፋ፣ ደህንነቱን የጠበቀና በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን መስራት ይገባል ብለዋል።


በመስክ ጉብኝቱ የጤና ሚኒስቴር፣ የክልል፣ የተጠሪ መስሪያ ቤቶች፣ የሆስፒታሎች እና አጋር ድርጅቶች አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።