የጤና ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ወጣቶች በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመተባበር በጤናው ዘርፍ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር በዛሬው እለት አካሂዷል፡፡
እውቅናውን የተሰጣቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች ሲሆኑ በቅዱስ አማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በአለርት ማእከል፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በጥሩነሽ ቤልጂንግ ሆስፒታል፣ በካቲት 12 ሜዲካል ኮሌጅ፣ በራስ ደስታ ሆስፒታል እና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ ወስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ወጣቶች ናቸው፡፡
የእውቅና አሰጣጥ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ እንደ ጤና ሴክትር ብዙ ነገሮችን በገንዘብ እጥረት ምክንያት ማሳካት በማንችልበት አገር ውስጥ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የጤናው ዘርፍ በእወቀት ማነስና በአገልግሎት መስጠት ውስንነት ምክንያት ብዙ ሰዎች የሚንገላቱበት፣ ብዙ ጊዜቸውን የሚያጠፉበት፣ የጤና ጉዳት እስከ ማድረስ የሚስተዋልበት ዘርፍ መሆኑ ጋር ተያይዞ እናንተ ይህን ዘርፍ የምትረዱ በመሆናችሁ ምስጋና ይገባችኋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ይህን በጎ ፍቃድ ለማድረግ ጊዜያችሁን በማዋላችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል፡፡ በቀጣይ በጎነትን የሚያጎሉ ስራዎችን ተጠናክረው እንደሚሰሩም ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ገልጸዋል፡፡
የበጎ ፍቃድ ስራ የአንድ ወቅት ሳይሆን የሁል ጊዜ ስራ ነው ያሉት በጤና ሚኒስቴር የሰው ሃይል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ሳሙኤል፣ ዛሬ ማህበረሰቡን መርዳት አለብን በሚል የተለያዩ አገልግሎቶችን ስትሰሩ ለቆያችሁ ወጣቶች ምስጋና የሚሰጥበት ቀን ሲሆን የዚህ አካል በመሆናችሁም እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመድረኩ የየሆስፒታሎቹ የ2013 ዓ.ም የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ለበጎፍቃደኛ ወጣቶቹም የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰቷል፡፡