"የጤና መድህን አባላትን ቁጥር በማሳደግ የዜጎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጡ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ

  • Time to read less than 1 minute
lia

አገር አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2014 ዓ.ም ዕቅድ ግምገማ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የስራ አቅጣጫ የሰጡት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ እንደተናገሩት የጤና መድህን አባላትን ቁጥር በማሳደግ የዜጎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጡ ስራ በ2014 በጀት ዓመትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡


የጤና መድህን አባላትን ቁጥር በማሳደግና ዘላቂነት ያለው የፋይናንስ ስርዓትን በመፍጠር በጤና ተቋማት ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚረዳ የገለጹት ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ ይህንን ለማሳካትም ከላይ እስከታች ያለው የጤና መዋቅር አመራር በመደጋገፍና በቅንጅት መንፈስ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡


ዶ/ር ሊያ ታደሠ አክለውም በጤና ተቋማት የሚነሳውን የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍም የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ከትንበያ እስከ ስርጭት ያለውን አሰራር ለማሻሻል የተለያዩ ሪፎርሞችን ተግባራዊ እያደረገ ስለመሆኑና በዓለም አቀፍ አቅራቢዎች የተፈጠረውን እጥረትም ለመፍታት የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማጠናከር በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡


የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው የ2014 በጀት ዓመት የአባላት ማፍራትና የዕድሳት ማቀጣጠያ ሰነድን ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ መሰረትም የጤና መድህንን ሲተገብሩ የነበሩ 834 ወረዳዎችን ወደ 914 ማድረስ እና 58 በመቶ የነበረውን የአባላት ቁጥር ወደ 68 በመቶ ማሳደግ የሚሉ ግቦች ተቀምጠዋል፡፡


በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ በ2013 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ቅርንጫፎች የሰርተፊኬትና የዴስክ ቶፕ ኮምፒዩተር ሽልማት ከጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሠ ተቀብለዋል፡፡ ደሴ፣ አዳማ፣ አርባምንጭ፣ አሶሳ እና አዲስ አበባ ቅርንጫፎች ከየክላስተራቸው የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ የተሸለሙ ሲሆን ሁሉም የክልልና የከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎችም የአመራር ሚናቸውን ስለተወጡ ተመሳሳይ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡