የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሀገራችን ያለበትን ሁኔታና በኮቪድ-19 ክትባት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሀገራችን የወረሽኙ ምጣኔ በአንፃራዊ ሁኔታ ከነበረበት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሯ ካለፉት 3 ሳምንታት ጀምሮ ግን በሳምንታዊ ሪፖርት በበሽታው የመያዝ መጠን በ 4 እጥፍ ጭማሪ፣ በጽኑ የሚታመሙ ሰዎች በ2.5 እጥፍ ጭማሪ፣ ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖች ደግሞ በ2.8 እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱንና ይህም አሳሳቢ እንደሆነ ገልፀዋል።
ነገር ግን በሀገራችን ወረርሽኙን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች ትግበራ እየቀነሰ በመምጣቱ በሌሎች በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እየተከሰተ ያለው ሦስተኛ ዙር የኮቪድ-19 በሽታ የስርጭት ማእበል ችግር በኢትዮጵያ እንዳይመጣ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከል አንዱ ዘዴ የሆነውን የክትባት ሂደት ባብራሩበት ወቅትም ወደ ሀገር የሚገቡ ክትባቶች በአይነት የተለያዩ ቢሆኑም በሽታውን ከመከላከልና በበሽታው ሊደርስ የሚችለውን የከፋ ህመምና ሞት ከመቀነስ አንጻር ተመሳሳይ ዉጤት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም በአዲስ አበባ ካለዉ ከፍተኛ የኮቪድ ወረርሽኝ አንጻር ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የኮቪድ-19 ክትባት ላልወሰዱና እድሜያቸዉ ከ35 ዓመት በላይ ለሆኑ የሚሰጥ ሲሆን በተቀሩት ክልሎችና ከተማ አስተዳደር እድሜያቸዉ ከ55 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባም ሆነ በሁሉም ክልሎች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑና ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸዉ ሁሉ የክትባት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም በስራቸው ባህርይ ከብዙ ሰዎች ጋር ቀጥተኛ የሥራ ግንኙነት ያላቸዉ ሰራተኞችና የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮችና የጎዳና ተዳዳሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የመንግሥት ጤና ተቋማት በአዲስ አበባ ከነሀሴ 7 ጀምሮ እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ከነሀሴ 14 ጀምሮ እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡