የጤናና ጤና ነክ ተቋማት እና ባለሙያዎች ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈፃሚ

መግቢያ

የጤናና ጤና ነክ ተቋማት እና ባለሙያዎች ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈፃሚ የተቋቋመው በፌደራል መንግስት ስር የሚገኙ የጤናና ጤና ነክ ተቋማትንና ባለሙያዎችን በመቆጣጠር፣ የጤና ባለሙያዎችን ብቃት በመመዘን፣ የክልል ጤና ተቆጣጣሪ አካላትን በማብቃት ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት ነው። መሪ ሥራ አስፈፃሚው በስሩ 04 (አራት) ዴስኮች ያሉት ሲሆን እነዚህም የብቃት ምዘና ፈተና ዝግጅት እና አስተዳደር ዴስክ፣ የጤና ባለሙያዎች ብቃት ምዘና ሬጂስትራር ዴስክ፣ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ምዝገባ፣ ፈቃድና ቁጥጥር ዴስክ እና የጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዴስክ ናቸው።

ራዕይ

ደህንነቱ የተጠበቀ እና ከፍተኛ ጥራት ያለው የጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ሙያዊ ብቃት እና ሥነ-ምግባር ባላቸው የጤና ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ ሲደርስ ማየት

ተልዕኮ

በጤናና ጤና ነክ ተቋማት እና ባለሙያዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ፣ የጤና ባለሙያዎችን ብቃት በመመዘን፣ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማረጋገጥ፣ በትብብር በመስራት እንዲሁም ወቅታዊ የቁጥጥር መረጃ  በመስጠት ደህንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ፡፡ 

ዓላማዎች

  1. የቁጥጥር ህጎችን በማስከበር እና ብሔራዊ የጤና ተቋማት ደረጃዎችን በመተግበር የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ
  2. የቁጥጥር ህጎችን በማስከበር እና ብሔራዊ የጤና ነክ ተቋማት የሀይጅንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ደረጃዎችን በመተግበር የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ
  3. የጤና ባለሙያዎችን ብቃትና ስነ ምግባር ማረጋገጥ

ተግባርና ኃላፊነት

  1. በፌዴራል መንግስት ስር ያሉ የጤና ተቋማትን መቆጣጠር (የቅድመ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ማካሄድ፣ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መስጠትና ማደስ፣ የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ማካሄድና የተገኙ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ መከታተልና አስፈላጊ ሲሆን አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ)
  2. በፌዴራል መንግስት ስር ያሉ የጤና ነክ ተቋማት (ዩኒቨርሲቲ፣ ማረሚያ ቤት፣ የስድተኛ መጠለያ ካምፕ፣ ከአራት ኮከብ በላይ የሆኑ ሆቴሎችና በዓለም አቀፍ ኤርፖርት ውስጥ የሚገኙ የምግብ እና መጠጥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት) ላይ የኃይጅንና አከባቢ ጤና አጠባበቅ ቁጥጥር ማካሄድ እንዲሁም የተገኙ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ መከታተልና አስፈላጊ ሲሆን አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ
  3. ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ብሄራዊ የጤናና ጤና ነክ ተቋማት ደረጃዎች እንዲዘጋጁና እንዲከለሱ መደገፍ
  4. የጤናና ጤና ነክ ተቋማት ራሳቸውን በራሳቸው የሚቆጥጠሩበት ስርዓት መዘርጋት
  5. ሀገራዊ የጤና ተቋማት መረጃ በዳታ ቤዝ (Master Facility Registry) እንዲመዘገብ ማድረግና የተሟላ ሀገራዊ መረጃ እንዲኖር ማድረግ
  6. ከውጭ ሀገር የሚመጡ የጤና ባለሙያዎችን መመዝገብና የሙያ ፈቃድ መስጠት
  7. በመላ ሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎችን ምዝገባና የሙያ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደት መቆጣጠር
  8. ከተግባር ትንተና በሚመነጨው የፈተና ፍኖተ ካርታ በመመስረት የብቃት ምዘና  ፈተናዎችን ማዘጋጀት
  9. ለጤና ባለሙያዎች የብቃት ምዘና ፈተና መስጠት
  10. የቁጥጥር ስርዓቱን በኮምፒውተር የታገዘ እንዲሆን ማስተባበር
  11. የክልል ጤና ተቆጣጣሪ አካላትን አቅም መገንባትና ድጋፍ ማድረግ (ስልጠና መስጠት፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ)
  12. ብሔራዊ የቁጥጥር ሕጎች (አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ ጋይድላይን፣ ማኑዋል፣ ወዘተ.) እንዲወጡ ማመቻቸት እና የእነዚህን ሕጎች አፈጻጸም ማረጋገጥ
  13. የቁጥጥር ህጎችን እና በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ተዋናዮችን መብቶች እና ግዴታዎችን የማስተዋወቅ ሥራ መስራት