ደሴ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወደ አገልግሎት አሰጣጥ በመመለሱ መደሰታቸውን ተገልጋዮች ገለፁ
በጦርነቱ ምክንያት ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ የህክምና አገልግሎት መስጠት በጀመረው የደሴ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግልጋሎት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ነዋሪዎች ገለፁ።
በሆስፒታሉ ሲገለገሉ ያገኘናቸው ወ/ሮ መሬሞ ሙሄ እና አቶ አበበ አብረሀም እንደገለፁት የሆስፒታሉ በሮች ተከፍተው ነጭ ገዋን የለበሱ የጤና ባለሙያዎች በፈገግታ ታካሚዎችን ሲያስተናግዱ በማየታቸው ተደስተዋል።
ህዳር 25/ 2014 ዓ ም በሆስፒታሉ እንድትገኝ ከሀኪሟ ቀጠሮ ተሰጥቷት እንደነበርና በነበረው ጦርነት ምክንያት እንዳላቀረበች የተናገራቸው መሬሞ ያ የስቃይ ጊዜ አልፎ ዛሬ ወደ ሆስፒታሉ በመቅረብ ተመርምራ መድሀኒት ሊታዘዝላት በመቻሉ ከጭንቀት እንደገላገላት መስክራለች።
እህቴን ለማሳከም መጥቼ ተገቢውን አገልግሎት አግኝቼ የራጅ ምርመራ ውጤት እየጠበቅን ነው ያለው አበበ በበኩሉ ለዚህ ብርሀናማ ቀን በመብቃታችን ፈጣሪንና መንግስትን አመሰግናለሁ ብሏል።