እኤአ በ2030 የቲቢ በሽታን ለመግታት ቀጣይነት ባለዉ የልማት ግብ የተያዘዉ ዕቅድን ለማሳካት ተገቢዉን ትኩረት ሳያገኝ የቆየዉ የህጻናትና አፍላ ወጣቶች የቲቢ በሽታ ልይታ፣ ምርመራና ህክምና ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት ያስፈልጋል።
የኢፌድሪ ጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሎሜ ቶጎ እየተካሄደ ባለዉ 72 ኛው የአፍርካ አህጉር የአለም ጤና ድርጅት መድረክ ላይ እንደገለጹት በኢትዮጵያ በ2015 የጸደቀዉ የህጻናትና አፍላ ወጣቶች የቲቢ በሽታ ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ህጻናትና አፍላ ወጣቶችን ከቲቢ በሽታ የመከላከልና ህክምና ስራ መሻሻሉን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተሰራዉ ስራ በበሽታዉ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም የቲቢ በሸታ እንዲሁም የቲቢ -ኤች አይቪ ጫና አሁንም ከፍተኛ በሆነባቸዉ 30 አገሮች አንዷ መሆኗን ያወሱት ዶ/ር ሊያ፣ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚሰሩ ስራዎች ለቲቢ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑና የተዘነጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።